የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የልማት አቅጣጫ ለመውሰድ ምቹ ሀኔታ ይፈጥራል-የጁቡቲ ሉአላዊ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስሊም ፌሪያኒ

130

ጥቅምት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የልማት አቅጣጫ ለመውሰድ ምቹ ሀኔታን እንደሚፈጥር የጁቡቲ ሉአላዊ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስሊም ፌሪያኒ ያላቸውን እምነት ገለጹ፡፡

የፌደራል መንግስቱና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የደረሱትን የሠላም ስምምነት ያደነቁት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ስምምነቱ በተለይ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የሠላም ስምምነቱ የኢንቨስትመንት ስራዎች በተሳለጠ መልኩ የሚተገበሩበትን ምቹ እድል እንደሚፈጥርም ነው ያብራሩት፡፡

የጁቡቲ ሉአላዊ ፈንድ በዋናነት የጁቡቲን ኢኮኖሚ ለማስፋት ያለመ መርሃ ግብር ሲሆን፤ ከወደብና መርከብ ጭነት አገልግሎት በተጨማሪ ቁልፍ የሚባሉ ዘርፎች እንደ ቴሌኮም ፣ቴክኖሎጂዎች ፣የኃይል፣ ቱሪዝም፣ መሰረተ ልማቶች፣ኢንዱስትሪ ልማቶችን ያካተተ ነው።    

መርሃ ግብሩ ከሁለት ዓመት በፊት በጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡማር ጌሌ ይፋ የተደረገ ሲሆን ለተግባራዊነቱም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ ታውቋል።

የፈንዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስሊም ፌሪያኒ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ጠንካራ ስትራቴጂካዊ  አጋርነት ያላቸው አገራት ናቸው።

ይህ አጋርነታቸው ጠንካራ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያነሱት።    

የጀቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ ኢንቨስትመንት ከጀቡቲ ባለፈ በሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ አንዷ መዳረሻ ናት ብለዋል። 

የጀቡቲ ሉዓላዊ ፈንድ 60 በመቶ ከጅቡቲ ውጭ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነውን መዋዕለ ንዋይ በኢትዮጵያ ለማፍሰስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጁቡቲ ሉአላዊ ፈንድ አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ በምን መልኩ መስራት እንችላለን የሚለውን ቅኝት እያደረግን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለአብነትም በኢንዱስትሪ፣በቤቶች ግንባታ፣በግብርና ቱሪዝምን፣ቴሌኮም፣በሃይል በመሳሰሉ ዘርፎች ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት መኖሩንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ በአየር፣ባቡርና በመንገድ መሰረተ ልማት መተሳሰራቸውን አስታውሰው፤ይህም የቀጣናውን የኢኮኖሚ ውህደት መፋጠን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡  

በኢትዮጵያ በሆቴል ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም አገራቱ በጋራ ሊሰሩበት የሚችሉት ሌላኛው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ከጅቡቲ ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ በፈንዱ አማካኝነት ኢንቨስት ማድረግ ሲሆን ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንቱ መዳረሻ ናት።         

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም