መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አገራት እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ

701

ጥቅምት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አገራት እንዲያግዙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጥሪ አቅረበዋል።

የሰላም ስምምነቱን  አስመልክቶ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፃ ተደርጓል።

ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሂደት ምን መልክ እንዳለው አብራርተዋል።

በዚህም የተኩስ ማቆም፣ ትጥቅ ማስፈታት፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም፣ መሰረታዊ አገልግሎት ማስጀመር፣  መልሶ ግንባታንና የመሳሰሉ ጉዳዮች የስምምነቱ  አንኳር ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል።

በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬትለማውረድ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ገልፀዋል።

በስምምነቱ መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት  ወታደራዊ አመራሮች የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ወታደራዊ አመራሮቹ በቀጣይ ቀናቶች  በኬንያ  ናይሮቢ  ተገናኝተው  ስምምነቱን  ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በማብራሪያቸው መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልፀው እስካሁን ባለው ሂደት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ወዳጅ አገራት ምስጋና ቸረዋል።

መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አገራት እንዲያግዙ አምባሳደር ሬድዋን ጥሪ አቅርበዋል።

ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱ መካከል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፤በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስና በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ዳን  የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚያመጣ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ስምምነቱ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ምስክርነት የሰጠ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም  ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።