በኢትዮጵያ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለማህበረሰቡ ምን ውጤት አስገኙ?

523

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ጥቅምት 26/2015  በኢትዮጵያ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለማህበረሰቡ ምን አተረፉ? ምንስ አስተማሩ?

ከማህበረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች አንዱ የሆነው የተፋሰስ ስራ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እና በግብርና ምርት ስርዓቶች ላይ ለሚተገበሩ የስነ-ምህዳር ሂደቶች (አግሮ ኢኮሎጂ) ውጤታማነት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በራስ ገዝነት የሚንቀሳቀሰው የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል አንጋፋው ባልደረባ አቶ ወረታው አበራ ለበርካታ አስርት ዓመታት በተፋስስ ስራዎች ላይ በባለሙያነትና በኋላፊነት ሰርተዋል።

በኢትዮጵያ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የተፋሰስ ጥበቃ ስራዎች በስፋት በዘመቻ ሲሰሩ ቢቆዩም በተጠቃሚው እና አስፈጻሚው አካል ያለው መናበብ የላላ በመሆኑ የተደከመውን ያህል ውጤታማ አልነበሩም ይላሉ።

ችግሩን ለመቀረፍም የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ከሰባት ዓመት በፊት የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ማህበረሰቡን ያቀናጀ 'የመማሪያ ተፋሰስ' የተሰኘ ፕሮጀክት ይዞ ወደ ስራ መግባቱን ይገልጻሉ።

'መማሪያ ተፋሰስ' ትግበራም በቴክኖሎጂ በተደገፈ፣ ማህበረሰቡን በባለቤትነት ባሳተፈ መልኩ በተለያዩ ክልሎች በጥናት በተለያዩ ንዑስ ተፋሰሶች ገቢራዊ ተደርጎ ውጤታማ ሆኗል ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማነትን በተመለከተ ህብረተሰቡን የማሳመን ስራዎች መሰራታቸው፣ ከአርሶ አደሩ፣ ከፖለቲካ አመራሩና ከልማት ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋቱና፣ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች መጠናከር መቻላቸው ለውጤቱ መገኘት ተጠቃሽ ናቸው።

በሰባት ዓመታት 'የመማሪያ ተፋሰስ' ስራዎች 1 ሺህ 212 በጓሮ ልማት፣ 890 በጉድጓድ ውሃ እንዲሁም 700 ሰዎች በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በተሻሻሉ የእንስሳት እና ሰብል ዝርያዎች አቅርቦትም ሰፊ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን በዚህም በእንስሳት ሀብት ልማት 900፣ በሰብል ምርት ማሻሻል 1 ሺህ 900 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።

50 ሺህ ሜትር ኪዩብ ኮምፖስት ማዘጋጀት መቻሉንም ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን ጥቅም በመረዳቱ የፕሮጀክቱ ጊዜ ቢጠናቀቅም አርሶ አደሩ ስራውን አስቀጥሏል ብለዋል።

ዕድርና መሰል ማህበራዊ አደረጃጀቶች በተፈጥሮ ሀብትና ተፋሰስ ጥበቃ ስራዎች እንዲሳተፉ በመደረጉ ለማህበረሰቡ ትልቅ ትምህርት መስጠት መቻሉንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የተፋሰስ ልማት ስራዎች መንግስታዊ መዋቅሩን ጨምሮ ከባለሙያ እስከ አርሶ አደሩ ሁሉንም አስተምሯል ነው ያሉት።

አርሶ አደሮች በመማሪያ ተፋሰስ ምን ተምረዋል የሚለውን ኢዜአ ማዕከሉ ከሰራባቸው ተፋሰሶች መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫና ደቡብ ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮችን አነጋገሯል።

አርሶ አደር አለኸኝ ደምለው በሰሜን ሜጫ ወረዳ 'የብራቃት ተፋሰስ' እንዲሁም አርሶ አደር 'ጨቅሌ ፈንቴ' በደቡብ ሜጫ ወረዳ የደብረ ያዕቆብ ተፋሰስ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ናቸው።

አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት ማህበረሰቡን ባሳተፈ አግባብ በተሰሩ ስራዎች የተራቆቱ ደኖች አገግመዋል፣ የተጋጋጡ እና የተጎራረዱ የወል መሬቶች ከመሸርሸር ድነዋል፤ ምንጮችም ጎልብተዋል።

አርሶ አደሮቹ ከልቅ ግጦሽ የተጠበቁ የወል መሬዎች ላይ መኖ በማልማት፣ ከብቶቻቸውንም አስረው በመመገብ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በእርከንና መሰል የተፋሰስ ስራዎችም ምርታማነትን ማሳደግ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማትም የገበያ ሰብሎችን ማልማትና አመጋገባቸውን ማሻሻል እንደቻሉ አረጋገጠዋል።

ሂደቱ አልጋ በአልጋ ባይሆንም የወል መሬቶችና የተከለሉ ደኖችን ከልቅ ግጦች በመጠበቅ ዕድርን መሰል ባህላዊ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ጥብቅ የቁጥጥር ስርአት እንዳዳበሩ አንስተዋል።

በዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ስራዎችን ጥቅም በመረዳቱ የአስተሳስብ ለውጥ ስለማምጣቱ ነው የሚመሰክሩት።

በተፋሰሱ ነዋሪ አርሶ አደሮች ከብት አስሮ መመገብ በመቻላቸው የመኖ እጥረት ስለመቀረፉ፣ እንሰሳትን አድልቦ በመሸጥም ውጤታማ መሆናቸውን ከተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል የሆነው ወጣት ዘላለም ጨቅሌ ይናገራል።

ከዚህም ባለፈ በችግኝ ጣቢያዎችና በሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ብዙ ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ ስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው አድርጓል ብለዋል።

የወል መሬቶችን በመከለል ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ ውጤታማ ከመሆን ባለፈም የወል መሬቶችን ለተደራጁ ወጣቶች በመስጠት በአቮካዶና ሌሎች ፍራፍሬ ልማት ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ።

ወጣት ምህረት መብርሃቱና ጓደኞቹ በ2006 ዓ.ም ተደራጅተው የተረከቡትን የወል መሬት በአቮካዶ በማልማት ትርፋማ ከመሆን አልፈው አቮካዶ ልማት በአካባቢው እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነዋል።

ወጣቶቹ በቀጣይ የአቮካዶ ልማት ከማጠናከር ባሻገር የኦቮካዶ ችግኝ አዳቅሎ በመሸጥም የግብርና ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋፋት ፍላጎት እንዳላቸው የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ምህረት ይናገራል።

ወጣቶቹ ሌሎች መሰል ልማት ላይ ያልዋሉ የወል መሬቶችን ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት መለወጥ ከተቻለ የአገሪቷን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያገዛል የሚል እምነትም አላቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም