ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሳይበር ደህንነት ላይ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው- አስተዳደሩ

151

ባህርዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር በመደገፍ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስገነዘበ።

በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 10ኛውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ሶካ በኮንፈረንሱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ በቴክኖሎጂና በሳይንስ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም ላይ ለዲጅታል ኢኮኖሚና ኢንቨሰትመንት ልዩ ትኩረት በተሰጠበት በዚህ ዘመን እየተስተዋለ ያለው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ስጋት መከላከል ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

አስተዳደሩ በአገሪቱ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከ10 ዩንቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የትብብር ስራው ውሱን የሆነውን የተቋሙን የሰው ሃይል ለማሰልጠንና ዩንቨርሲቲዎች በሚያካሂዷቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትን ማረጋገጥን ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲመራመሩ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሃንስ በበኩላቸው "የአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከመንግስት ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የዛሬ አስር አመት የተቋቋመው አካዳሚው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ፣ በማሰራጨትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

አካዳሚው የዘርፉን ምሁራን በአባልነት በማቀፍ የእርሰ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ እውቀትና ክህሎት የሚገበያዩበት መድረክ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ ከዓለም ጋር የሚወዳደር ዕድገት ለማስመዝገብ ከፖሊሲ ማማከር እስከ ምርምር ድረስ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩንቨርሲቲው በዓለም ላይ ተፈላጊ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት የሰው ሃይል ወደ ውጭ በመላክ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በማሪታይም አካዳሚ የመርከብ ቴክኒሻኖችን፣ ኢንጅነሮችንና በተለያዩ የመርከብ ሙያ ከ2ሺህ በላይ የሰው ሃይል በማሰልጠን በዓለም የመርከብ ድርጅቶች በማስቀጠር ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሌሎች የትምህርት ዘርፎችም በርካታ የሰው ሀይል በማሰልጠን ለአገርና ለዓለም አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመው "በቀጣይም ገበያውን መሰረት በማድረግ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።  

የኢንስቲቲዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ቢምረው ታምራት በበኩላቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት፣ ምርምር በማካሄድና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በትስስር በመስራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በየዓመቱ በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ምሁራን የተሰሩ ችግር ፈች የምርምር ስራዎች ለውይይት በማቅረብ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም