የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው-ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ

139

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ተናገሩ፡፡

የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኢሉሴጉን ኦባሳንጆ ለኢዜአ እንድተናገሩት፤ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የሰላም ስምምነት ግጭትን በማስቆም ለዘላቂ ሰላም መስፈን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡

ስምምነቱም ችግሮችን በዘላቂነት በውይይት እንዲፈቱ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም አካላት ለተፈጻሚነቱ ጥበብ በተሞላበትና በአገር ወዳድነት ስሜት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ሲካሔድ የቆየው ውይይት የኢትዮጵያ ህዝቦችን የጋራ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ስምምነቱ በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ሁለት የታጠቀ ሀይል ሊኖር እንደማይችል ያስቀመጠ ሲሆን፣ የህወሓት ታጣቂዎችም ትጥቅ የሚፈቱ ይሆናል።

በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎት እንዲጀመርም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም