የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥታ የምትሰራ መሆኑን ያረጋገጠ ነው-በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር

126

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 25/2015 በኢፌዴሪ መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥታ የምትሰራ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አሊዪ ገለጹ።

አምባሳደር ፈይሰል አሊዪ ከኢዜአ ጋር በበየነ መረብ በነበራቸው ቆይታ የተደረገው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት እያከናወነች ላለው ልማት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የሄደችበትን ርቀት ያሳየ ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከግጭት ይልቅ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እስከመጨረሻው ድረስ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት የነበረውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን አምባሳደሩ አንስተዋል።

የተደረገው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲያዊ ውይይት ቅድሚያ በመስጠት የምትሄድበትን ታሪካዊ ዳራ ያሳየ መሆኑን በማስታወስ።

በዚህም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያላትን አቅም የሚያሳይና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሊማሩበት የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ምን ጊዜም ለሰላም ንግግር ቅድሚያ በመስጠት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ያገኘችበት መሆኑን አስረድተዋል።

ስምምነቱ የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ የመስጠት የምንጊዜም አቋሟን ያሳየችበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተደረገው የሰላም ሂደት ውጤታማነት ችግር ለመፍጠር ዘመቻ ከፍተው ለነበሩ አካላት ህብረቱም አህጉራዊ ጉዳዮችን የመፍታት አቅም እንዳለው አሳይቷል ነው ያሉት።

አምባሳደር ፈይሰል የኢትዮጵያን መረጋጋት፣ ሰላምና ብልጽግና የማይፈልጉ አካላትን ሴራም ያከሸፈ መሆኑን በመጠቆም።

በቀጣይም በግጭቱ በተጎዱ አካባቢዎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር፣ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ተቋማትን፣ መንገድና ሌሎች የመልሶ ግንባታዎች ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም