በመኽር ወቅቱ በ270 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የዘር ብዜት እየተካሄደ ነው-ማዕከሉ

209

ደሴ (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 በመኽር ወቅቱ በ270 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የተለያዩ ሰብሎች ዘር ብዜት እያካሄደ መሆኑን የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያካሄደ ያለውን የማሽላ ዘር ብዜት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዛሬ የመስክ ጉብኝት አካሂዷል።

የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አካሉ ገብሩ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን በማረጋገጥ በቂ ምርት ለገበያ እንዲያቀርብ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ማዕከሉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በማላመድና በማባዛት፣ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን በማሻሻል፣ በበሽታና ነፍሳትን በመቆጣጠር የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሻሻልና ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ 64 የተለያዩ ሰብሎች ላይ ባካሄደው ምርምር ውጤታማ በመሆናቸው ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በማሽላ፣ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በማሾና በገብስ ሰብሎች ላይ እየተካሄደ ካለው የዘር ብዜት ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል ።

የብዜት ስራው በአማራ ክልል የሚያጋጥመውን የዘር እጥረት ከማቃለል ባለፈ ምርታማነትን ለማሳደግ ድርሻው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

"የሚባዛው ዘር ውጤታማ ነው" ያሉት አቶ አካሉ በሚቀጥለው ሳምንት ሰብሉ ተሰብስቦ ምርቱ በጊዜያዊ ዘር ማቆያ መጋዝን ይገባል" ብለዋል።

የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲሱ ቡላ በበኩላቸው አርሶ አደሩ በተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችና ዘር እጥረት በድካሙ ልክ መጠቀምና የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ ሳይችል መቆየቱን አውስተዋል።

ከሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው።

"ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን አርሶ አደሩን በምርምር ለማገዝ እየሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ከሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር  በመሆን የተለያዩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማላመድና በማባዛት ለአርሶ አደሩ ዘር እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።

በዳዋ ጨፋ ወረዳ የጉር ቀበሌ ነዋሪና በማሳቸው የተሻሻለ የማሽላ ዘር ከሚያባዙ አርሶ አደሮች መካከል  ሰይድ አህመድ  በሰጡት አስተያየት "አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑና ፈጣን ዘር ባለማግኘታችን የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ሳንችል ቆይተናል "ብለዋል።

ከዚህ በፊት የሚዘሩት ማሽላ ዝርያ ለመድረስ እስከ ስምንት ወር  ይወስድ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት ዘር በሶስት ወር መድረሱን ተናግረዋል።

ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳ  ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቁመው "በዝርያው ምርታማነታችን በእጥፍ ያድጋል" ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም