የኢትዮጵያና የሶማሊያ የመረጃ ተቋማት ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚያከናውኗቸውን የጋራ ስምሪቶች አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ

122

ጥቅምት 25/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያና የሶማሊያ የመረጃ ተቋማት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እየተስፋፋ የመጣውን ሽብርተኝነት ለመከላከል የሚያከናውኗቸውን የጋራ ስምሪቶች አጠናክረው ለመቀጠል ስምምነት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ የተመራ ልዑክ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በሶማሊያ ከተፈጸመው የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች የሚደርሱ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተላኩ የሕክምና መሣሪያዎችንና መድሐኒቶችን ይዞ ወደ ሶማሊያ ተጉዟል፡፡

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ከመርሐ ግብሩ ጎን ለጎን ከሶማሊያ አቻ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ማሐድ ሞሐመድ ጋር በወቅታዊና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በውይይቱ ወቅት ሰሞኑን በሶማሊያ ሞቃዲሾ በደረሰው የሽብር ጥቃት የተሰማቸውን ሐዘን መግለጻቸውን ያመለከተው መግለጫው፤ እንደዚህ አይነት ክስተቶችን ለማስቀረት በምሥራቅ አፍሪካ የሚደረጉ የጸረ ሽብር ትግልን የተመለከቱ አጋርነቶችንና ትብብሮችን ማጠናከር እንደሚገባ መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከሶማሊያ አቻው ጋር ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ በአቅም ግንባታ መስኮችና በመረጃ ልውውጥ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል።

ከሰሞኑ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ መንሥኤዎቹንና መፍትሔዎችን በተመለከተ ጥናት የሚያከናውንና ለሀገሪቱ መንግሥት እገዛ የሚያደርግ ቡድን በመላክ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

የሶማሊያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ኤንድ ሴኩዩሪቲ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ለተደረገው እገዛ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡

ሽብርተኝነትን የመከላከል ስምሪቶች የተቀናጀ እንቅስቃሴ የሚፈልጉ በመሆናቸው በምሥራቅ አፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን ሥጋት ለመመከት ቁልፍ አጋር ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን መናገራቸው ተመልክቷል፡፡

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር የድንበር አካባቢ የጸጥታ ሁኔታዎችን በማሻሻልና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን በማሳደግ ረገድ የደረሱባቸው ስምምነቶች ተግባራዊ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም