መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን የሚያስተዋውቁ ሞጋች ጋዜጠኞችን ለማፍራት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል

666

(ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ እና ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን የሚያስተዋውቁ ሞጋች ጋዜጠኞችን በማፍራት ለሀገር ግንባታ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ዘርፍ አመራሮች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም፣ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ እያበረከተች ያለውን ጉልህ አስተዋጽኦ በአግባቡ ለዓለም ማህበረሰብ ማስረዳት የመገናኛ ብዙሃኑ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ነው አመራሮቹ የተናገሩት።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሠ ቱሉ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ሚና ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

መገናኛ ብዙኃን በአሁኑ ወቅት ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠር ጎን ለጎን የሙያ መመሪያዎችን በማጠናከር እንዲሁም የኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን ተፈጻሚነት በመቆጣጠር ለሀገር ግንባታ የሚያግዙ ስራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራትም የኢትዮጵያን ገፅታ በአግባቡ መገንባት አለባቸው ነው ያሉት አመራሮቹ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ፤ ዓለም አቀፉ የሚዲያ ኢንዱስትሪ በደረሰበት ደረጃ አቅምን ማሳደግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስገንዘብ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቷን ለማስከበር መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው የላቀ ነው ይላሉ።

ስለሆነም ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚሞግቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

ለዚህም የዓለም መገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ማሟላት እንደሚገባቸው በማንሳት።

አንጋፋዎቹ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ለግል ሚዲያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግና ልምዳቸውን በማካፈል ማጠናከር  አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው የሚዲያ ተቋማት ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ በሀገር ግንባታ ረገድ በርካታ ተልዕኮ እንዳላቸው አንስተዋል።

በመሆኑም ሀገራዊ ሚናቸውን በአግባቡ በመወጣት የተሳሳቱ ትርክቶችን እያስተካከሉ ኢትዮጵያን የሚያጸኑ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለዘመናት ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ዛሬ ላይ መድረሷን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁንም የተስፋ ጎዳናዋን ስትጀምር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጫናዎች እየተሞከሩባት መሆኑን አንስተዋል።

ባለብዙ መልክ ጫናዎችን ተቋቁማ እንድትሻገር መገናኛ ብዙሃን ለእውነታዋ መሞገት፣ ለዓለም እያበረከተች ያለውን ሚና በግልፅ ማሳወቅ አለባቸው ነው ያሉት።

ከዚህም ባለፈ፣ታሪኳን ከፍ በማድረግ የቱሪዝም እሴቷን በማስተዋወቅ ገፅታዋን መገንባትም የመገናኛ ብዙሃኑ የቤት ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል።