የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት 2ኛ ዓመት የመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት አካሄዱ

259

ጥቅምት 24/2015 (ኢዜአ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት በማስመልከት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።

ጥቅምት 24 ፤ 2013 ዓም የኢትዮጵያ ህልውናን አደጋ ውስጥ በማስገባት ለውጭ ጠላት ተጋላጭ እንድትሆን በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ዒላማ ያደረገ ጥቃት የተሰነዘረበትን ዕለት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት የጥቃቱ 2ኛ ዓመት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል ።

የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ “ለኢትዮጵያ የከፈላችሁትን አንረሳውም” የሚል መልዕክት መድረኮችን በማዘጋጀት የተዘከረ ሲሆን በጥቃቱ መስዋትነት የከፈሉ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም አባላትን ለመዘከር የህሊና ጸሎት ፣ የሻማ ማብራትና የፓናል ውይይት ተካሂዷል ።

በመታሰቢያ ሥነሥርዓቱ የፀጥታና ደህንነት አካላት የሀገር ሉዓላዊነት እንዲከበር የከፈሉትንና እየከፈሉ ላሉት ውድ መስዋእትነት የላቀ ክብርና ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባም ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም