የአሜሪካ መንግስት በሰላም ስምምነቱ የተገኘውን መልካም እድል በመጠቀም በኢትዮጵያ መጻኢ እድል ገንቢ ሚና መወጣት ይኖርባታል -የአሜሪካ ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ

383

ጥቅምት 24/ 2015 (ኢዜአ ) የአሜሪካ መንግስት በፌደራል መንግስና ሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የተገኘውን መልካም እድል በመጠቀም በኢትዮጵያ መጻኢ እድል ገንቢ ሚና እንድትወጣ ‘የአሜሪካ ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’(ኤፓክ) የተሰኘው የፖለቲካ ተግባር ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ

“የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በ ኢኮኖሚ ፣ማህበራዊና፣ዴሞክራሲ መስኮች ወደ ጀመረቻቸው የማሻሻያ ስራዎች ትኩረቷን እንድትመልስ ያደርጋታል” ሲል ገልጿል።

የዘላቂ ግጭት ማቆም ዜና አስደሳችና መልካም የሚባል መሆኑን የኤፓክ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተገኑ ገልጸዋል።

በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት በአገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሕዝቡን የስቃይ ስሜት መጋራታቸውን አንስተዋል።

“የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከአራት ዓመት በፊት በማህበራዊ፣ዴሞክራሲና ኢኮኖሚ መስኮች ወደ ጀመረቻቸው የማሻሻያ ስራዎች ትኩረቷን እንድትመልስ ያደርጋታል” ነው ያሉት።

የአሜሪካ መንግስት በፌደራል መንግስትና ሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የተገኘውን መልካም እድል በመጠቀም በኢትዮጵያ ቀጣይ መጻኢ እድል ላይ ገንቢ ሚና ትወጣለች ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ትብብር በጋራ መከባበር መርህና ግንኙታቸውን ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሂደት ጽኑ እምነት ነበረው ያሉት አቶ መስፍን ለኢትዮጵያ በትጋት ሲሰሩ ለነበሩ ሁሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ወደ ሰላም የምታደርገውን ጉዞ እየተወጣ ያለውን ገንቢ ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ኤፓክ ይህ እንዲሳካ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልጸዋል።