በአዳማ ከተማ ከ300 ሺህ ዶላር በላይ ከሀገር ለማስወጣት የሞከረ አሽከርካሪ መያዙን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ

429

አዳማ ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ ከ300 ሺህ በላይ ዶላር ከሀገር ለማስወጣት የሞከረ አሽከርካሪ መያዙን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መመሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል እንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለፁት አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ገንዘቡን በኮድ 3/89158 ኢ.ት በሆነ ሎቤድ መኪና ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በስውር ደብቆ ሲያጓጉዝ ነው።

በአዳማ ከተማ ዳቤ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ዳቤ ሶሎቄ ኬላ ፍተሻ ላይ የተያዘው የገንዘብ መጠንም 302ሺህ 400 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።

በብሔራዊ ደህንነትና በአዳማ ከተማ የፀጥታ ሃይሎች ትብብር በ23/2/2015 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ላይ የተያዘው ገንዘቡ ወደ ውጭ ሃገር በሚጓዝ የኮንቴይነር ጭነት ስር በስውር ቦታ ተደብቆ መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።

የመኪናው አሽከርካሪም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በምርመራ ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል።