የኢንተርኔት አገልግሎት ለማከፋፈል ከስምንት ድርጅቶች ጋር የተደረገው ውል አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ያስችላል

3820

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 ኢትዮ ቴሌኮም ሰሞኑን ከስምንት ድርጅቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያከፋፍሉ ያደረገው ውል አገልግሎቱን እንደሚያቀላጥፍለት ገልጿል።

 ቴሌኮሙ   የኢንተርኔት አገልግሎትን ለደንበኞች ለማከፋፈል እንዲያስችል ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፈቃድ ከተሰጣቸው ስምንት ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት አድርጓል።

አገልግሎቱን ለመስጠት ጂቱጂ የተባለ ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎች ሰባት ድርጅቶች ጋር “ቨርቹዋል የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች” በሚል አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ተዋውሏል።

በኢትዮ ቴሌኮም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ውሉ ድርጅቶቹ የኢንተርኔት አገልግሎትን ከኢትዮ ቴሌኮም በመውሰድ ለደንበኞች በቀላል ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችላቸው ነው።

ድርጅቶቹ ከኢትዮ ቴሌኮም 100ና ከዚያ በላይ ሜጋ ባይት የኢንተርኔት አገልግሎት እየወሰዱ ለተገልጋዩ እንደሚያቀርቡ አቶ አብዱራሂም አስታውቀዋል።

እንደ አቶ አብዱራሂም ገለጻ፤ ፈቃድ የሚሰጣቸው ድርጅቶች የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ያስቀመጠውን መስፈርት በማሟላት በብቃት ለደንበኞች አገልግሎቱን የሚያቀርቡ ድርጅቶች ናቸው።

በዚህም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው፣ ብቁና አስፈላጊው የሰው ሃይልና በጀት እንዲሁም በዘርፉ በቂ ተሞክሮ ያለው ማንኛውም ድርጅት አገልግሎቱን መስጠት እንደሚችል ጠቁመዋል።

 ይህ ቨርቹዋል የኢንተርኔት አገልግሎት የተሰኘውን አገልግሎት የሚሰጡት ኩባንያዎች በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የተዘረጋውን የኢንተርኔት መስመር ብቻ የሚጠቀሙ ይሆናሉ።

በአገሪቱ በአጠቃላይ 16 ነጥብ 8 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘ መረጃ ያመላክታል።