በዞኖቹ ከ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተከናውነዋል

61
ሚዛን መስከረም 15/2011 በቤንች ማጂና በባሌ ዞኖች በክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚተመኑ ተግባራት መከናወናቸውን የዞኖቹ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያዎች አስታወቁ። አገልግሎቱ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥልም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል። በክረምት ወራት ከተሰጠው አገልግሎት በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ወጣቶች 11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር፤ በደቡብ ክልል የቤንች ማጂ ወጣቶች  ደግሞ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር  የሚገመቱ ሥራዎችን አከናውነዋል። የባሌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተክሌ በዞኑ 2010 የበጎ ፈቃድ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ወጣቶችና ተቋማት እውቅና ለመስጠት በተዘጋጀ መርሐግብር ላይ እንደተናገሩት በዞኑ በአገልግሎቱ ከ252 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ ወጣቶቹ ካከናወነቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም መለገስ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ቤት መስራትና ጥገና ይገኙበታል። አቶ ሰለሞን እንዳሉት ሥራውን በክረምት ወራት ብቻ ሳይሆን በበጋውም ለማስቀጠል በተያዘው በጀት ዓመት አካል ሆኖ በመደበኛነት ይሰራል ብሏል፡፡ በዞኑ ክረምት እየተጠበቀ የሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቋሚነት የሚካሄድበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጠይቀዋል፡፡ አገልግሎቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከማቃለል በላይ፤ በዜጎች መካከል መተሳሰብን በመፍጠር ካለው ፋይዳ አኳያ ዘላቂነት እንዲኖረው ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ በመሳተፍ የዋንጫ ተሸላሚ ከሆኑት ወረዳዎች መካከል  የሰዌና ወረዳ ተወካይ ወጣት ሀሰን ኡስማን እንዳለው የአካባቢያቸውን ወጣቶች በማደራጀት በክረምቱ ወራት ተጨማሪ ትምህርት በመስጠት፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤቶችን በማደስ ባደረጉት እንቅስቃሴ ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡ በአገልግሎቱ  የተሳተፉ የወረዳው ወጣቶች ባከናወኑት ተግባር የህሊና እርካታ እንዳገኙም ገልጿል፡፡ አገልግሎቱ በቋሚነት አንዲከናወን  ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል የሚል እምነት እንዳለውም ወጣት ሀሰን ተናግሯል፡፡ በበርበሬ ወረዳ በመርሐ ግብሩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ  መሳተፉን የተናገረው ወጣት አህመድ ሱፊያን ደግሞ  በአገልግሎቱ ተሳትፎ  ሰዎችን መርዳት በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ነው የገለጸው። "በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ጓደኞቼን በማስተባበር ኃላፊነቴን ለመወጣትም ተዘጋጅቺያለሁ" ብሏል፡፡ በሰዌና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አብዱረህማን ሰኢድ በበጎ ፈቃደኛ  አገልግሎት ወጣቶች  አማካይነት በክረምት ወቅት የተሰጠውን የማጠናከሪያ ትምህርት መከታተሉን ተናግሯል፡፡ ትምህርቱም በሚቀጥለው ዓመት ለሚወስደው ብሔራዊ ፈተና ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ገልጾ፣  አገልግሎቱ ተማሪዎችን  ተጠቃሚ ስለሚያደርግ በቀጣይነት እንዲጠናከርም ጠይቋል፡፡ ወይዘሮ ፋጡማ አብደላ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የአካባቢያቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ''የፈረሰ የሳር ክዳን ቤቴን  በቆርቆሮ ክዳን በመቀየር ህይወቴን አቃንተውልኛል'' ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የቤንች ማጂ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰዒድ ኢብራሒም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት በዞኑ10 ወረዳዎች የሚኖሩ ከ42ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ  ወጣቶች  በልማት ሥራዎች  አስተዋጽኦ አድርገዋል። ወጣቶቹ በጤና፣ ትምሀርትና ማህበረሰብ ልማትን ባካተቱ ከ20  በላይ ዘርፎች እንደተሳተፉም ተናግረዋል። በአገልግሎቱ የተሳተፉት ወጣቶች ማህበረሰቡን በልማት ሥራዎቻቸው ከመደገፋቸው ባሻገር የዕረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪው ወጣት ግርማ ከበደ በበኩሉ የክረምት ዕረፍት ጊዜውን በሚኖርበት ሻይ ቤንች ከተማ ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ሆኖ በችግኝ ተከላና በጽዳት ሥራዎች መሰማራቱን አስታውሷል። የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ኪዳኔ መርሻ በበኩላቸው ወጣቶቹ ምንጮችን ከብክለት በመጠበቅ ፣ የተዘጉ ቦዮችን በመክፈትና የአቅመ ደካማሞችን በመርዳት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም