ኢትዮጵያን በልማት ወደ ከፍታዋ ለማሻገር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን - አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ

105

ጥቅምት 23/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በልማት ወደ ከፍታዋ ለማሻገርና የተቃጡባትን ጫናዎች ሁሉ በመመከት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ከደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳውና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በጎፋ ዞን ጉብኝት አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጠላቶቻችን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን  ጦርነት በመመከት ሉአላዊነታችንን አስከብረናል ነው ያሉት።

ትግሉ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ያነሱት አፈጉባኤው፤ በኢኮኖሚው መስክም የተቃጣብንን ጫና ለመቀልበስ ኢትዮጵያውያን ቆርጠው መነሳት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ጎፋ ላይ የአገር መሪ ጉብኝት ሲያደርግ ከ54 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን በማስታወስ፤ አካባቢው የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ማብቀል የሚችል እምቅ አቅም እንዳለው አንስተዋል፡፡

የመንግስት ከፍተኛ መሪዎች በጎፋ ጉብኝት ያደረጉበት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን ለማጽናት በግብርናው ክፍል ኢኮኖሚ ላይም በትኩረት መስራት እንዳለብን ለማሳየት ነው ብለዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማፋጠን፤ ኢትዮጵያ በምግብ ሰብል ራሷን እንደምትችልና የተረጂነት ታሪኳን እንደምትቀይር የምናሳይበት ትልቅ ምዕራፍ ላይ ነን ነው ያሉት።

በዚህም ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ካለችበት ፈተና ወደ ወደ ከፍታዋ እናሻግራታለን ነው ያሉት።

አፈጉባኤው አክለውም የጎፋ ህዝብ ሀገሩን ለማጽናት ዋጋ መክፈሉን በማስታወስ በልማቱም አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ጎፋ ዝናብ አጠር ቢሆንም አካባቢው ምርታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካባቢው በበቆሎ ምርትና በእንስሳት ሃብቱ በስፋት እንደሚታወቅ በመጠቆም፡፡ 

ህብረተሰቡ ህይወቱ ተቀይሮ ከራሱ አልፎ ለአገር የሚበቃ ትርፍ ምርት በማምረት እንዲጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአርሶ አደሩንና የኢንቨስተሩን አቅም በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም