የተቋሙን የመፍትሄ እርምጃዎች ያልፈጸሙ ኃላፊዎች በወንጀል ሊጠየቁ ነው

65
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያስተላለፋቸውን የመፍትሄ እርምጃዎች ያልፈጸሙ የስምንት ተቋማት ኃላፊዎች በወንጀል እንዲጠየቁ ለፍትህ አካላት ማቅረቡን አስታወቀ። በተቋሙ የዋና እንባ ጠባቂ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀንዓ ሶና ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ ከሕብረተሰቡ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመመርመር አስተዳደራዊ በደል መፈጸማቸው ሲረጋገጥ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ ውሳኔ ያስተላልፋል። ተቋሙ ባለፉት 10 ወራት ባካሄደው ክትትል ውሳኔዎቹን ለመፈጸምና ለተቋሙ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ በደቡብና በአማራ ክልሎች የሚገኙ የስምንት ተቋማት ኃላፊዎች በወንጀል እንዲጠየቁ ለፍትህ አካላት ማቅረቡን ተናግረዋል። የተቋማቱ ኃላፊዎች የፈጸሙት አስተዳደራዊ በደልም ከመሬት ይዞታና ሰራተኞችን ያለአግባብ ከስራ ከማሰናበት ጋር በተያያዘ መሆኑን አመልክተዋል። አቶ ቀንዓ እንደገለጹት ባለፉት 10 ወራት ተቋሙ በ1 ሺህ 360 አስተዳደራዊ በደሎች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን መርምሯል። ምርመራ ከተካሄደባቸው አቤቱታዎች 714ቱ በአስፈጻሚ አካላት አስተዳዳራዊ በደል መፈጸሙ በመረጋገጡ እንዲታረሙ ከእነ መፍትሄ ሀሳባቸው ለሚመለከታቸው ተቋማት ቀርበዋል። በተቋሙ ውሳኔ መሰረት አብዛኛዎቹ ተቋማት ውሳኔዎቹን የፈጸሙ ሲሆን 38 ተቋማት ግን ባለመፈጸማቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ሪፖርት መቅረቡንና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከነዚህ ውስጥ ስምንቱ ምንም አይነት ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው ሲደረግ ቀሪዎቹ ከክትትሉ በኋላ ምላሽ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከሕብረተሰቡ ከሚቀርቡ አቤቱታዎች ውስጥም አብዛኛዎቹ የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ፣ የመሬት ይዞታ፣ የሰራተኞች ደረጃ ዕድገት፣ ዝውውርና ከቅጥር ጋር በተያያዘ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎትና ምላሽ ያለማግኘት ቅሬታዎችን አንስተዋል። ስለ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተልዕኮና ተግባር የሕብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ የአቤቱታ አቅራቢዎች ቁጥር መጨመሩን አቶ ቀንዓ ገልጸዋል። ተቋሙ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በስምንት ከተሞች ቅርንጫፎችን በመክፈቱ ለህብረተሰቡ አቤቱታዎችን  የተሻለ መንገድ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል። የሕብረተሰቡ አቤቱታ የማቅረቢያ መንገድም ከአካል ባለፈ የስልክ፣ ኢ-ሜይል፣ ፋክስ አማራጮችን የመጠቀም ልምዱ እየዳበረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም