ለመብራት አገልግሎት መጀመርም ሆነ ለሰላማዊ ህይወት ላበቃን መከላከያ ሰራዊታችን ትልቅ ክብር አለን…የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች

85

ወልዲያ ጥቅምት 23/2015(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በወረራው ካደረሰው ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አገግመን ለመብራት አገልግሎትና ለሰላም እንድንበቃ ላስቻለን መከላከያ ሰራዊታችን ትልቅ ክብር አለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት በደረሰባቸው አከባቢዎች የሰው ነፍስ ከማጥፋት በተጨማሪ ለህዝብ አገልግሎት የሚውለውን መሰረተ ልማት ማውደም የቆየ ባህሪው ሲሆን በወረራ በያዛቸው የአማራና አፋር ክልሎችም ያደረገው ይኸው ነው።

አሸባሪው በወረራ ከያዛቸው ስፍራዎች አንዱ ሆነው ቆቦ አካባቢ በአገር መከላከያ ሰራዊቱ ጀግንነት ከወራሪው ነጻ ከወጣ በኋላ ላፍታም ሳይቆይ ነው የመብራት መስመሩ ጥገና ተደርጎ አገልግሎቱ የተጀመረው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢቢው ነዋሪ የወደሙ የመሰረተ ልማቶች በፍጥነት እየተጠገኑ ለአገልግሎት መብቃታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሲሳይ አቃኔ “አሁን ግን ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በወሰደው እርምጃ በአሸባሪው ቡድን የጭካኔ ድርጊት ሲፈጸምበት የነበረው አካባቢያችን ነጻ ከመውጣት ባለፈ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታችን አስደስቶናል” ብለዋል።

“የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ሃገር ለሚያድነው መከላከያ ሰራዊታችን ትልቅ ክብር አለኝ” የሚሉት ነዋሪው፤ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅም ከመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መኮንን አስናቀ በበኩላቸው ቆቦ ነጻ ከወጣች ጀምሮ ሌሊትና ቀን በመስራት በዚህ ፍጥነት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ስላደረገን ለመንግስት ምስጋና ይድረሰው ብለዋል።። 

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ የሠራዊት አባላት የፈጸመው አስከፊ ጥቃት በሚዘከርበት ዋዜማ ላይ የመብራት ተጠቃሚ መሆናቸው ልዩ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሰኢድ አባተ እንዳሉት አሸባሪው ቡድን በደረሰበት ሁሉ የህዝብ መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።

በዚህም የቆቦና አካባቢው የመብራት መሰረተ ልማቱ በመውደሙ በጨለማ ውስጥ እንደቆየ ጠቁመው ሰሞኑን መስመሩን በመጠገን ከተማዋ የመብራት ተጠቃሚ እንድትሆን ተደርጓል ብለዋል።

ለዚህም የህዝቡን ችግር የተረዱ የመብራት ሃይል ሰራተኞች ሌሊትና ቀን በመልፋት አካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻላቸው አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም