ፍርድ ቤቱ በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

456

አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ተጠርጥረው በማረፊያ ቤት በሚገኙት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ ሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተጠራው ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት አቀነባብረዋል በሚል በተጠረጠሩት  አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ ይገኛል።

በደህንነት ቢሮ አመራር የነበሩት የእኚህ ሰው ጉዳይ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው እለት ታይቷል።

ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ እንዳስረዳው በተፈፀመው የቦንብ ጥቃት የሰው ህይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል።

አክሎም ጥቃቱ ከባድና የተቀነባበረ  ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮችም አሁንም ድረስ እየቀረቡ ስለሆነ  ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪው አቶ ተሰፋዬ ኡርጌ  በበኩላቸው “መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም ሥራውን ግን በማከናወን ላይ አይደለም”  በማለት ለችሎቱ ተናግረዋል።

በመሆኑም የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢነት የለውም በማለት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

የፍርድ ሂደቱ እየተጓተተ ነው ያሉት ተጠርጣሪው ጉዳያቸው በአፋጣኝ እንዲታይላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱም  ፖሊስ ቀሪ ምርመራ ማካሄድ ይችል ዘንድ የጠየቀውን የሰባት ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

ጊዜው የተፈቀደው የወንጀሉን ክብደትና ውስብሰብነት  ከግምት በማስገባት መሆኑንም አመልክቷል።

በዚህ መሰረት ፖሊስ በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ በማጠናቀቅ ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን የምርመራ ውጤት ለመስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።