በአመለካከት፣ በክህሎትና በስራ ባህል የዳበረ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል-ሚነስቴሩ

188

ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) ምርታማነትን የሚያሳድግና በአመለካከት፣ በክህሎት እንዲሁም በስራ ባህል የዳበረና ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ለማፍራት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በወጣቶች የስራ ዕድልና ክህሎት ላይ ባደረገው የጥናት ውጤት ላይ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አድርጓል።

ጥናቱ በኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ስርዓት አሁን ካለው የገበያ ፍላጎት ጋር ያለውን መስተጋብር በመዳሰስ የፖሊሲና ስትራቴጂ ምክረ-ሀሳብ አመላክቷል።

ጥናቱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ ዶክተር አማረ ማተቡ፤ ገበያው የሚፈልገው ክህሎትና በትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት አለመጣጣም መኖሩን በጥናት እንደተገኘ አመላክተዋል።

ለአገር ምጣኔ ሃብት ሽግግርና ለማህበረሰብ ቀረጻ ትምህርትና ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጥናቱ ውጤት መጠቆሙን በማንሳት።

የመንግስት ተቋማት ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል በማፍራት፣ ቀጣሪ ድርጅቶችም የተግባር ስልጠና ለመስጠት ችግሮችን በፖሊሲና ስትራቴጂ መፍታት እንደሚገባ በጥናቱ ምክረ-ሀሳብ ላይ ተጠቀየሟል።

የስራና ህክሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ጥናቱ ችግሮችን ለይቶ ያስቀመጠና  መፍትሄዎችን ያመላከተ በመሆኑ ለቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫዎች መነሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ቢኖርም ድርጅቶች የሚፈልጉትን ክህሎት የተላበሰና ብቃት ያለው የሰው ሃይል በብዛት አለመኖሩንም ገልጸዋል።

በመሆኑ የትምህርት፣ ምርምርና ሌሎች ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

መንግስት በዕውቀቱ የተካነና ክህሎት የተላበሰ እንዲሁም አመለካከቱ መልካም የሆነ ትውልድ በመፍጠር ስራ ፈጣሪነት፣ ታታሪነት፣ የይቻላል አመለካከት ያለው ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጨምረዋል።

ምርታማነትን የሚጨምር፣ ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል፣ አገር ያላትን ሃብት ተጠቅሞ ለዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ትውልድ ለመፍጠርም የስራና ህክሎት ሚኒስቴር ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የቀረቡ የፖሊሲና ስትራቴጂ ምክረ ሃሳቦች ዝርዝር ዕቅድ ተዘጋጅቶላቸው የሚጠበቀውን ለውጥ እንደሚያመጡ ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም በስራ ላይ ያሉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማገናኘት በምርምርና ጥናት በመዳሰስ ምክረ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም