ለኢትዮ-ኤርትራ የጋራ እድገት የሰላም ግንኙነቱ መጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ተገለጸ

60
መቀሌ  15/1/2011 የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በጋራ ለማደግ ሁለቱ ሃገራት የጀመሩት የሰላም ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ኤርትራዊያን ገለጹ። ኤርትራዊያኑ በመቀሌ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችንና የመሰረተ ልማት ስራዎችን ትላንት ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ላይ አራት ልጆቻቸውን ይዘው ከአስመራ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ርግአት ዕቁባይ እንዳሉት፣በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠሩ ፋብሪካዎች በመቀሌ ከተማ በማየታቸው ተደስተዋል። በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ልማትና እድገት በትውልድ ሃገራቸው ኤርትራ ውስጥ እንዲደገም በሁለቱም ሃገራት መካከል የተፈጠረውን የሰላም መንገድ እንዲጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። በአስመራ ከተማ የጋራጅ ባለቤት የሆነው ወጣት ዳኒኤል ገብረመስቀል በበኩሉ መቀሌ በሁሉም የልማት ዘርፎች በተለይም በማንፋክቸሪንግ በኢንዳስትሪ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች ለኤርትራዊያን አርዓያ እንደሚሆኑ ተናግሯል። "ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ፈጣን ነው፤ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት እያስመዘገቡ ነው" ያለው ወጣቱ ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። "በትጋትና በትክክል ከሰራን በፍጥነት ማደግና መለወጥ እንደሚቻል በመቀሌ ከተማ ካየኋቸው የኢንዳስትሪ የልማት ተቋማት መመልከት ችያሉሁ፣ተቋማቱን በማየቴም ደስተኛ ነኝ" ያሉት ደግሞ የ80 ዓመት የእድሜ ባለፀጋው አቶ ሰሎሞን ገብረታትዮስ ናቸው። "የኤርትራ ወጣቶች የተከፈተውን የሰላም በር በአግባቡ በመጠቀምና ተመልሶ እንዳይዘጋ በመጠበቅ አብረው ሊሰሩና ሊያድጉ ይገባል" ብለዋል። ኤርትራዊያኑ በተቋማቱ ተገኝተው እንዲጎበኙ ያስተባባረው የመቀሌ ከተማ የማንፋክቸሪንግ ልማት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዘርኡ አስፈሃ እንደተናገሩት በከተማው ውስጥ ከ1 ሺህ 480 በላይ ሰዎች በማንፋክቸሪንግ ኢንዳስትሪ ልማት ዘርፍ ብቻ ተሰማርተዋል። "በሁለቱም ሃገራት መሪዎችና ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተከፈተውን የሰላም በር ማስቀጠል ከቻልን ሁላችንም በጋራና በፍጥነት ማደግ እንችላለን" ብለዋል። የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካና በአንድ የህንድ ባለሃብት በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተቋቋመው ዘመናዊ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በእለቱ በኤርትራዊያኑ ተጎብኝተዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም