ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ለግልና አካባቢ ንጽህና ትኩረት መስጠት ይኖርበታል

199

ጎባ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በንጽህና ጉድለት ሳቢያ የሚከሰቱ የተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ለግልና ለአካባቢ ንጽህና ትኩረት መስጠት እንደሚኖርበት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ የጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አበራ ቦቶሬ በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ የኮሌራ በሽታ የተከሰተባቸው አካባቢዎችን ጎብኝተዋል።

ኃላፊው በዞኑ ሶስት የአርብቶ አደር ወረዳዎች የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየተደረጉ የሚገኙ የመድሃኒትና የኬሚካል አቅርቦት ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

ምክትል ኃላፊው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ክልሉ ተላላፊ በሽታዎች ስርጭትን ለመከላከልና ለመግታት ለግልና አካባቢ ንጽህና ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

በክልሉ መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ኤክስቴንሽን ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በህብረተሰቡ መሰረታዊ ጤና ላይ መሻሻሎች ቢኖርም አሁንም ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

''በተለይ እንደ ኮሌራ የመሳሳሉ በቀላሉ መከላከል በምንችላቸው ተላላፊ በሽታዎች ህይወት እየጠፋ መሆኑ ለዚሁ ማሳያ ነው'' ብለዋል፡፡

ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ለግልና ለአካባቢ ንጽህና ትኩረት መስጠት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን መሀመድ በኩላቸው፤ ጽህፈት ቤቱ የኮሌራ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የበሽታው ምልክት የታየባቸውን ሰዎች የክልሉ ጤና ቢሮ እና አጋር ድርጅቶችን ባሳተፈ መልኩ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮሌራ በሽታ ክትባትና ሌሎች የህክምና አገልግሎት ብቻ በመስጠት በሽታውን መቆጣጠር አይቻልም ያሉት ሀላፊው፤ ሕዝቡ የግልና የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

በዞኑ በርበሬ ወረዳ ሀምበላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ ከድር በሰጡት አስተያየት የግልና የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ በሽታውን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

''በቀበሌያችን የተመደቡት የጤና ኤክስቴሽን ሰራተኞች የሰጡን ትምህርት በሽታው ለመከላከል አግዞናል'' ያሉት ደግሞ ሌላዋ የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ ኢብራሂም ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም