በዞኑ በበጋ ወራት በመስኖ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

1251

አምቦ መስከረም 15/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን በበጋ ወራት በመስኖ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ መስኖ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተክሌ ኢዶሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ 103 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ በማልማት ለማግኘት እየተሰራ ነው።ዕቅዱ ባለፈው ዓመት ከተመረተው ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ይኖረዋል።

የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በሁለት ዙሮች በሚከናወኑት የመስኖ ልማት ሥራዎች 274 ሺህ አርሶ አደሮች ቀጥተኛ ተሳታፊዎችና ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

በዚህም አርሶ አደሮቹ የዝናብ ውሃ በማቆር፣ በዘመናዊ መስኖ ታግዘው በፓምፕ ውሃ በማውጣትና አነስተኛ ጉድጓዶችን በመቆፈር  ልማቱን እንደሚያከናውኑም አቶ ተክሌ ተናግረዋል።

በክረምቱ ወቅት 52 የማህበረሰብ ኩሬዎች ውሃ መያዛቸውንም አስታውቀዋል።

ለልማቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማቅረብም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ልማቱ ለተጨማሪ 50 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ገልጸዋል።

ኩሬዎቹ  ከመስኖ ስራው ጎን ለጎን ለዓሣ እርባታ ለማዋል መታሰቡንም ገልጸዋል።

የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ቤኩማ አራርሳ በሰጡት አስተያየት በመጪው የበጋ ወቅት ለሚካሄደው የመስኖ ልማትሥራ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን አነስተኛ ኩሬ በመቆፈር የውሃ ማቆር ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

አርሶ አደር ጉደታ መልካ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በአንድ በኩል የመኽር እርሻውን በመንከባከብ በሌላ በኩል ደግሞ በበጋ ወራት ለመስኖ ልማት የምናውለው ውሃ በበቂ መጠን ለማቆር ሙሉ ጊዜያችንን በሥራ እያሳለፍን እንገኛለን ብለዋል ።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የመስኖ ልማት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቶ እንደነበር የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።