ብአዴን ሀገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥሉ አዳዲስ አመራሮችን ወደፊት ማምጣት ይጠበቅበታል….የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች

2115

ደብረ ማርቆስ/ደብረ በርሃን/ደሴ መስከረም 15/2011 የአማራ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የተጀመረውን ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ ዳር ለማድረስ የሚያስችሉና የህዝብ ድጋፍ ያላቸውን አዳዲስ አመራሮችን ወደፊት ማምጣት ይጠበቅበታል ሲሉ የደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ደሴ ነዋሪዎች ገለጹ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ የሆኑት አቶ ገበያው ተመስገን እንዳሉት ጉባኤው ብአዴን የስምና የአርማ ለውጥ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ፈትሾ ለማረም የሚዘጋጅበት እንደሚሆን ጠብቀዋል።

በተጨማሪም በህዝብና በድርጅቱ ስም የሚነግዱ አመራሮችን በማስወገድ በተማሩ ወጣቶችና የህዝብ ይሁንታ ባላቸው አዳዲስ አመራሮች በመተካት የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን መሰረት የሚጥልበት መሆኑንም ተናግረዋል።

“እስካሁን የብአዴን አመራር አካላት በዘመድ አዝማድና በጥቅም ትስስር የተደራጀ በመሆኑ ይህን ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም” ያሉት ደግሞ በከተማዋ የቀበሌ 01 ነዋሪ የሆኑት አቶ ኢሳይያስ ማንደፍሮ ናቸው።

“በወረዳና በዞን ተሹመው በህዝብ ላይ ግፍና በደል ሲፈጽሙ የነበሩ አመራሮች ተገምግመው መውረድ ሲገባቸው ይባስ ተብሎ ወደ ክልል በመውሰድ የተሻለ ሹመት የሚሰጥበት ሁኔታ በጉባኤው በግለጽ ተጣርቶ እልባት እንዲሰጥ እፈልጋለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ አዳሙ ደነቀው በበኩላቸው ብአዴን በሚያካሂደው 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው አቅምና ብቃት ያላቸውን አዳዲስ ወጣት አመራሮችን በደከሙ አመራሮች ይቀይራል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጉባኤ ተሞክሮ በመውሰድ ድርጅቱ ጎልቶ የሚወቀስበትን ለክልሉ ህዝብ መብትና ጥቅም መከበር ደንታ የሌላቸው አመራሮችን ገምግሞ ማስወገድ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

“የክልሉን ህዝብ አንድነት የሚያጠናክሩ፣ የአማራውን ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና ማንነት የሚያጎለብቱ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በወሰን ይገባኛል ምክንያት ብጥብጥና ሁከት ሊያስነሱ የሚችሉ ጉዳዮች ላይም በጉባኤው ቁርጥ ያለ ውሳኔ ብአዴን ያሳልፋል ብዬ እጠብቃለሁ’’ ብለዋል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ዘነበ ኮስትሬ በበኩሉ ኪራይ የሚሰበስቡና የህዝባቸውን ክብር አሳልፈው የሰጡ ነባርና የቀድሞ አመራሮችን አበጥሮ በመለየት በወጣት አመራሮች በመተካት ብአዴን ታሪካዊ ጉባኤ ያካሂዳል ብሎ እንደሚጠብቅ ተናግሯል፡፡

ብአዴን ለውጡን የሚያስቀጥል ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማካሄድ ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት የሚበጅ ውሳኔዎችን በቁርጠኝነት ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁ የገለጹት ደግሞ በደሴ ከተማ የሚኖሩት አቶ ሰሎሞን ኃይሉ ናቸው።

” በጉባኤው ብአዴን ላለፉት ዓመታት እየተስፋፋ የመጣውን የዘረኝነትና የጽንፈኝነት አስተሳሰቦችና አመለካከቶችን በማስወገድ ለህዝባዊና አገራዊ አንድነት የሚጠቅም አቅጣጫ ያስቀምጣል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል።

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ እንደሚጀምር የድርጅቱን መግለጫ ዋቢ በማድረግ ቀደም ሲል ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።