በክረምት ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እያደረግን ነው -የትግራይ ደቡባዊ ዞን አርሶ አደሮች

64
ማይጨው  መስከረም 15/2011 በክረምት ወራት ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን በትግራይ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ የደቡባዊ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ። በራያ አላማጣ ወረዳ የገርጀሌ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሞላ ግርማይ እንዳሉት በአካባቢያቸው የተተከሉ ችግኞች ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ ነፃ ሆነው እንዲጸድቁ በእንክብካቤ ስራ እየተሳተፉ ነው። ችግኞችን ለማስተዳደር በተዘጋጀ የአካባቢ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ነዋሪው ተወያይቶ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ ከስምምነት ላይ መድረሱንም ተናግረዋል። በወረዳው የታሕታይ ዳዩ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ንጉስ ታደሰ በበኩላቸው በአካባቢው የተተከሉት ችግኞችን ለመጠበቅ በህዝቡ የተወሰነው መተዳደርያ ደንብ በማህበራዊ ፍርድ ቤት እንዲፀድቅ መደረጉን ገልፀዋል ። በደንቡ ከሰፈሩ አንቀፆች መካከል ችግኝ በተተከሉባቸው ስፈራዎች በሚገቡ እንስሳት ላይ የተጣለ የገንዘብ መቀጮ እንደሚገኝበት ተናግረዋል ። በአሁኑ ወቅት የተተከሉ ችግኞችን በመኮትኮትና ውሃ በማጠጣት እንክብካቤ መጀመራቸውን አርሶአደር ንጉስ ገልፀዋል። በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ አቻምየለህ አሰፋ እንዳሉት በ2010 ክረምት ወቅት ለተተከሉ ከ26 ሺህ በላይ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው ። በዞኑ ከ102 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በ13 ሺህ የልማት ቡድኖች ተደራጅተው ለተተከሉ ችግኞች እንክበካቤ እያደረጉ መሆናቸውንም ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም