በጤና ኤክስቴንሽን ላይ የስራዎች መደራረብ በውጤታመነቱ ላይ ጫና ፈጥሯል

76
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 አዲስ የሚታወቁ በሽታዎች በሚፈጥሩት የስራ መደራረብ የጤና ኤክስቴንሽን ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። ችግሩን ለማስወገድም የጤና ኤክስቴንሽኑን አደረጃጀት የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው ለማወቅ የተቻለው። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች ቡድን መሪ አቶ ነብዩ ንጉሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና ኤክስቴንሽን ስራ በአገሪቱ ውጤታማ የነበረና ሌሎች የውጪ አገራትም ተሞክሮ የወሰዱበት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን በዚያ ልክ ውጤታማ እየሆነ አይደለም። ችግሩን ለመለየት በተካሄደው ዳሰሳም ጤና ኤክስቴንሽኑ ላይ በየጊዜው የሚጨመሩ የወቅታዊ ስራዎች መደራረብ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ለመለየት ተችሏል ብለዋል። ቴክኖሎጂው እያደገ ሲሄድና ያልታወቁ በሽታዎች እየታወቁ በመሄዳቸው ከሶስት ዓመት በፊት 16 የጤና ፓኬጅ ስራዎች የነበረ ቢሆንም  አዳዲስ በሚታወቁ በሽታዎች ምክንያት አሁን ላይ ፓኬጁ ወደ 18 አድጓል። እነዚህ የተጨመሩት ስራዎች በነበሩት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተሰራ ስለነበር በአብዛኘው የመከላከል ስራው እየቀነሰ እንዲሄድ አድርጎታል ስሉ አቶ ነቢዩ ተናግረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የ2010 የጤና ኤክስቴንሽን ስራ አፈፃፀም በሚጠበቀው ልክ እንዳልተፈፀመ ገልፀዋል።  ከዚህም ሌላ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት በጤና ኤክስቴንሽኑ ስራ ላይ በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ ያደረገ እንደነበር አቶ ነብዩ አስታውቀዋል።  ችግሩን ቀርፎ የቀድሞውን ውጤታማነት ለመመለስ የፕሮግራም ክለሳ ተደርጎ ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ቡድን መሪው አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥ ዋነኛ ችግር የሆነውን የስራ መደራረብ ለማቃለል የሰው ኃይሉን ማሳደግ ዋና መፍትሔ መሆኑንም ነው የሚገልፁት።  የጤና ኤክስትንሽን ባለሙያው ቁጥር ሲያድግ የመከላከል ስራው እየተሻሻለ ከመሄዱም ባለፈ አሁን ላይ በህብረተሰቡ ደረጃ ያለው ስራው በየትምህርት ቤቱም በተጨማሪነት ተሳትፎ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል። በአዲስ መልክ የተከለሰው ይህ ፕሮግራም በዚህ ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም