አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ጫና በምስራቅ አፍሪካ የበላይነት ለማግኘት ነው- ምሁራን

345

ወሎ/ጅማ ፣ጥቅምት 19/2015 ( ኢዜአ) አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ለአሸባሪው ህወሓት በመወገን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ተጽዕኖ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የበላይነት ለማግኘት ነው ሲሉ ምሁራን ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንደሚሉት አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ ወታደራዊ የበላይነት ማግኘት ይፈልጋሉ።

ለዚህ ደግሞ በቀጣናው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ጎልታ በምትታየው ኢትዮጵያን የማዳከም እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል።

በዚህም ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለውን ሉዓላዊነትን የማስጠበቅና ራስን የመከላከል እርምጃ ወዳልተገባ አቅጣጫ ለመውሰድ ነው ጥረት የሚያደርጉት ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ልማት ጥናት ትምህርት ክፍል ባልደረባ ዶክተር አሊዩ ውዱ እንዳሉት ሁኔታው ምዕራባውያን በምስራቅ አፍሪካና በቀጣናው የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ነው።

ዶክተር አሊዩ እንዳሉት ከሶስት ዓመት በፊት የተካሄደ ጥናትን በማጣቀስ ምዕራባውያን ምክንያት ካገኙ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የበላይነት ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ የሚፈጠሩ የወታደራዊ አቅም መጎልበት እንቅስቃሴዎችና የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ ለዚህ አመላካች ነው ይላሉ።

አገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት በእብሪት ጦርነት ከፍቶ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ ያለውን አሸባሪውን ህወሓት ደግፈው በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚጥሩት ለዚህ ነው ብለዋል።

”ሕወሓትም የነሱን ፍላጎት ለማሟላት ያለ የሌለ ሀይሉን ተጠቅሞ አገሩን ሲወጋ የከረመውም ለዚህ ነው” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።

”መንግሥት ህዝቡን አስተባብሮ ለአገሩ ሰላም የማስከበር የጸና አቋም እንዳለው ማሳየቱ ፍላጎታቸው እንደማይሳካ የሚያሳይ ነው” ሲሉም አስረድተዋል።

መንግሥት ለትግራይ ክልል ህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም ሲል በተደጋጋሚ የሰላም እጆቹን መዘርጋቱን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ይህን እውነታ ለመቀበል ፍላጎት አለማሳየታቸውም በቀጣናው ሌላ አጅንዳ እንዳላቸው ያመላክታልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰላሟ ዘላቂ እንዲሆን ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር የተጀመረው ንግግር ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መክረዋል።

መንግሥት የኢትዮጵያ ትክክለኛ እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማሳወቅ ባለፈ ለልማት ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ  ኢኮኖሚን ለማረጋጋት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ያሳዩትን አንድነትና ፅኑ አቋም ዓለም በትክክል እንዲገነዘበው ማድረግ  እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ በበኩላቸው  አሸባሪውን ህወሓት በእጅ አዙር እየደገፉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ አንዳንድ ምዕራባውያን ድብቅ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

እነዚህ አካላት ፍላጎታቸውን ለማሳካት በኢትዮጵያ ላይ እየሞከሩት እንዳለው አይነት ጣልቃ ገብነት በሌሎች ሀገሮች ላይ ፈጽመውት አፍርሰዋቸዋል ሲሉም አስረድተዋል።

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ጭምር ለዚህ እኩይ ዓላማ በግልጽ ተሰልፈው የሀሰት ትርክትን በመፍጠር የዓለም አቀፋን ማህበረሰብ እያደናገሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

”መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ተላላኪዎቹን በመታገል የምዕራባውያንን ተልዕኮ ማክሸፍ የሁላችንም ግዴታ መሆኑን በመረዳት መታገል አለብን” ብለዋል ዶክተር ታደሰ።

መንግሥት ለሰላም ያለውን ፅኑ አቋም በተደጋጋሚ በተግባር ማረጋገጡ የሚያበረታታና መቀጠል ያለበት መሆኑን አስገንዝበው፤ ሕዝቡም ለሀገር አንድነትና ለሰላም ያለውን ፅኑ አቋም እንዲያስቀጥል ምሁራኑ ጠይቀዋል።