የብዙሀን መገናኛ ተቋማት የህጻናት መብት ስምምነቶች እንዲታወቁ በማድረግ በኩል ሚናቸው ደካማ መሆኑ ተጠቆመ

2594

አዳማ  መስከረም 15/2011 በሀገሪቱ የሚገኙ የብዙሀን መገናኛ ተቋማት ዓለም አቀፍ የህጻናት መብት ስምምነቶች እንዲታወቁና ተግባር ላይ መዋላቸውን ከማረጋገጥ አንፃር ሚናቸው ደካማ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ያካሄደው  መሆኑም ተመልክቷል።

ጽህፈት ቤቱ ከኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎችና ከሚዲያ ተቋማት ለተወጣጡ ባለሙያዎች ያዘጋጀው የሁለት ቀን ዓውደ ጥናት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጽህፈት ቤቱ የጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ አህመድ መሀመድ ህጻናትን ታሳቢ ያደረጉ የሚዲያ ፕሮግራሞች ውጤታማነትና ተግዳራቶችን አስመልክቶ የተካሄደውን የይዘት ቅኝት ትንተና ሰነድ ለመድረኩ ተሳታፊዎች አቅርበዋል ።

ባለሙያው በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ደቡብና ትግራይ ብዙሀን መገናኛዎች፣ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ፣ በኢቢሲና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ልጆችና ህፃናትን አስመልክተው የተላለፉ ዘገባዎችና ፕሮግራዎች የተቃኙበትን ጥናትና ዝርዝር ግኝቶች በመድረኩ ላይ ይፋ አድርገዋል ።

የተጠቀሱት ተቋማት ባለፉት ስድስት ወራት 45 ፕሮግራሞችና 8 ዘገባዎችን ቢያስተላልፉም ከሳቢነት፣ ከአስፈላጊነት፣ ከጥልቀት፣ ከጥራት፣ ከአካታችነት፣ ከግልጽነትና ከወቅታዊነት አንፃር ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ተጠቁመዋል።

ጥናቱ የተለያዩ ብዙሀን መገናኛ ተቋማት ሥራ ኃላፊዎችና የፕሮግራም አዘጋጆችን በመጠየቅ መካሄዱን የገለጹት ባለሙያው፣ ተቋማቱ በአብዛኛው ቋሚ የሆነ የህጻናትና ልጆች ፕሮግራም እንደሌላቸውና እንደትርፍ ሥራ የሚቆጥሩት መሆኑን በጥናቱ መረጋገጡን ገልጸዋል።

የህጻናቱ ጉዳይ ትኩረት ያልተሰጠው፣ እንደፕሮግራም ማሟያ ተደርጎ የሚወሰድበት አግባብ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ጥናቱ በልጆች ወይም በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃትም ሆነ ትንኮሳ እንዴት መከላከልና መቆጣጠር እንደሚቻል ተቋማቱ ማስተማር እንዳለባቸውም ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል።

የምርመራ ጋዜጠኝነትን ሥራ በመስራት አጥፊዎች በህግ አግባብ እንዲጠየቁ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አእንዳለባቸውም እንዲሁ አመልክቷል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ ብዙሃነትና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው “በእውቀት የዳበረና በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ሚና ወሳኝ በመሆኑ ጥናቱ የዳሰሳቸውን ተግዳራቶች ለመፍታት መረባረብ ይገባል” ብለዋል።

የህጻናትን መብትና ደህንነት የሚያረጋግጡ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ጽህፈት ቤቱ ማካሄዱን ጠቁመው፣ መድረኩ ጥናቱን በውይይት በማዳበር ለተግባራዊነቱ በቅንጅት ለመስራት ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው አውደጥናት ላይ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የኮሙዩኒኬሽንና የሚዲያ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።