ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ያላትን ጽኑ አቋም አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ያላትን ጽኑ አቋም አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ
ጥቅምት 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ያላትን ጽኑ አቋም አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።
አፍሪካም "ካዛብላንካ" እና "ሞኖሮቢያ" በተሰኙ ቡድኖች ተከፋፍላ ጉልበት እንዳይኖራት ሲደረግ የነበረውን እንቅስቃሴ በማስቆም የመጀመሪያውን የመተዳደሪያ ቻርተር በማዘጋጀት አህጉሪቷ አንድ ተቋም እንዲኖራት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች ብለዋል አምባሳደር ተስፋዬ፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ደግሞ የአህጉሪቷን የነጻነት ትግል ወደ ተሻለ ምእራፍ ያሸጋገረ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
በዚህም በወቅቱ ነጻ አገር የነበረችው ኢትዮጵያ ጸረ-ቀኝ ግዛት ትግል እንዲቀጣጠል የገንዘብ፣ የትጥቅ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ ለአህጉሪቷ ነጻነት አይተኬ ሚና ተጫውታለች፡፡
ለዚህ ደግሞ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪና የነፃነት ታጋዮ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ የዚምባቡዌ፣ የናሚቢያና ሌሎች የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮች ምስክሮች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ያላት ቁርጠኝነት የማይናወጥ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ፓን አፍሪካኒዝም እንደ ወሳኝ የፖሊሲ መርህ በማድረግ የአህጉሪቷ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰሩ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበትና የበረራ መዳረሻዎች ዝግ በሆኑበት ወቅትም አህጉሪቷ የወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ እንድታገኝ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
ይህም አህጉሪቱ ችግር በሚገጥማት ወቅት የኢትዮጵያ መሪዎች የመፍትሄው አካል ሆነው እንደሚቀጥሉ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥልም አፍሪካውያን የሚያሳዩት አጋርነት ኢትዮጵያ ለአፍሪካኒዝም መጎልበት ካላት ጽኑ አቋም የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ፓን አፍሪካኒዝም ጎልብቶ አፍሪካ በራሷ ጉዳይ የመወሰንና በዓለም አቀፍ ደረጃም የመወከል መብቷ እንዲረጋገጥ የሚደረገው የዲፕሎማሲ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።