በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የብርቅዬ ዱር እንስሳት ቆጠራ ተጀመረ

225

ጎንደር፣ ጥቅምት 18/2015(ኢዜአ) በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የብርቅዬ የዱር እንስሳትን ብዝሃ ህይወት ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስችል የቆጠራ ስራ መጀመሩን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ቆጠራው የተጀመረው በፓርኩ ክልል ውስጥ በጥናት በተለዩ 68 የቆጠራ ቦታዎች ነው፡፡

በዚህ ሳምንት በተጀመረው የዱር እንስሳቱ የቆጠራ ስራ በ32 የቆጠራ ቦታዎች የዋልያ ቆጠራ እንዲሁም በ36 ቦታዎች ደግሞ የቀይ ቀበሮዎች ቆጠራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቆጠራ ስራው 150 የሚሆኑ የፓርኩ ሱፐርቫይዘሮችና ስካውቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ልምድና ሙያ ያላቸው አጋር አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረው ቆጠራው በኮቪድና በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት አለመካሄዱን የገለጹት ሃላፊው፤ የአሁኑ የቆጠራ ስራ ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይ አስታውቀዋል፡፡

የቆጠራው ዋና አላማ የዱር እንስሳቱን አካባቢያዊ ስርጭት እንዲሁም የመኖሪያና የመመገቢያ ቦታዎች በመለየት አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ ለማድረግ ለማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል።  

በተጨማሪም የዱር እንስሳቱን የእድሜና የጾታ ስብጥር ጨምሮ የጤናቸውን ሁኔታና የመዋለድ ምጣኔያቸውን በጥናት የተደገፈ መረጃ ለማደራጀት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የቆጠራ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላም መረጃዎቹን በኮምፒውተር በማደራጀትና በመተንተን ውጤቱን ለአጥኚዎች፣ ለተመራማሪዎችና ለጎብኚዎች ይፋ የማድረግ ስራ ይመቻቻል ብለዋል፡፡  

ለቆጠራ ስራው የሚያስፈልገውን ወጪ በመሸፈን በኩል ከፓርኩ ጋር በቅንጅት የሚሰራው "አፍሪካን ዋይልድ ፋውንዴሽን" የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑንም እንዲሁ።

ድርጅቱ በፓርኩ ክልል በቱሪዝም ልማት፣ በአቅም ግንባታ፣ በፓርክ ማኔጅመንትና ስነ-ምህዳር ጥበቃ እንዲሁም በማህበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በዚህ ዓመትም ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው የፓርክ ልማትና ጥበቃ ስራዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መድቦ እየሰራ እንደሆነም ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡  

ፓርኩ ከሁለት ዓመት በፊት አካሂዶት በነበረው የዱር እንስሳት ቆጠራ የዋልያ ብዛት ከ900 በላይ፤ ቀይ ቀበሮ ደግሞ 75 ያህል እንደሚሆን ማረጋገጥ ተችሎ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

በፓርኩ ማንኛውም ዓይነት አደን የተከለከለና አስፈላጊው ጥበቃም የሚደረግለት መሆኑ ታውቋል።

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት / ዩኔስኮ/ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

በማራኪና ድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥ የታደለው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም