በተመቻቸላቸው የትምህርትና የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን በትግራይ ወጣቶች ተናገሩ

3637

መቀሌ ግንቦት 11/2010 በክልላቸው የተመቻቸውን የትምህርትና የስራ  እድል ተጠቅመው ውጤታማ መሆናቸውን በትግራይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው እስከ ከፍተኛ ትምህርት የሚደርሱ ተቋማት ተስፋፍተዋል፡፡

ከወጣቶቹ መካከል ረዳት ፕሮፌሰር  ሃፍቶም ከበደ በሰጠው አስተያየት መንግስት ባስፋፋው የትምህርት መሰረተ ልማት በአክሱም ዩኒቨርስቲ የባዮሎጂ መምህር ለመሆን መብቃቱን ተናግሯል፡፡

ሁለት ወንድሞቹም  በመቀሌ ዩኒቨርስቲ  ተማሪ እንደሆኑ ጠቅሶ ሁለት እህቶቹና ሌላ ወንድሙ ደግሞ በአክሱም የመሰናዶ ትምህትር ቤት  በመማር ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡

እራሱና ቤተሰቦች ለዚህ ስኬት መብቃት የቻሉት ባለፉት ዓመታት መንግስት  ለትምህርት መስፋፋት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ እንደሆነ ወጣቱ  ረዳት ፕሮፌሰር ተናግሯል፡፡

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከኤርትራ በ1996ዓ.ም. ተባርሮ መምጣቱን የሚናገረው ደግሞ የመቀሌ ከተማ  ነዋሪው ወጣት ኪሮስ ገብረፃድቃን ነው፡፡

ከአስመራ ተፈናቅሎ ሲመጣ በሰው ጋራዥ በሶስት ሺህ ብር ተቀጥሮ ስራ መጀመሩን አስታውሷል፡፡

ለወጣቶች በተመቻቸው የብድር አገልግሎት 100ሺህ ብር ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ በመበደርና የግሉን ገንዘብ በመጨመር አሁን የጋራዥ ባለቤት ለመሆን መብቃቱን ወጣት ኪሮስ ተናግሯል፡፡

ለመስሪያ ቦታ በተሰጠው 200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አሁን ለአስር ወጣቶችን የስራ እድል መፍጠሩ ጠቅሶ የበርካታ ወጣቶች የህይወት መስዋዕትነት ውጤት የሆነው የግንቦት ሀያ ድል የሀብትና የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡

በአክሱም ዩኒቨርቲ ሽሬ ካምፓስ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ከመሆኑ በተጨማሪ መንግስት ባመቻቸው ብድር ተጠቅሞ የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ባለቤት መሆኑን የተናገረው ደግሞ የሽሬ በእንዳስላሴ ከተማ ነዋሪው ወጣት ተማሪ ጎይቶም ታደሰ ነው፡፡