በደብረ ብርሃን ለችግረኛ ተማሪዎች ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

61
ደብረብርሃን መስከረም 14/2011 በደብረ ብርሃን ከተማ  ለ290  ችግረኛ ተማሪዎች ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ  የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገላቸው። በከተማው የሴቶች፣ ህጻናት፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት፣ወጣቶችና ባለሀብቶችና  እንዲሁም ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች አስተባባሪነት ድጋፉ የተሰጠው በከተማው ኢንዱስትሪ ፓርክ  ግንባታ ሳቢያ ለተነሱ ቤተሰቦች 200 ልጆች ነው። የደብረብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሽመላሽ ካሣሁን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፓርኩና ሠራተኞቹ ከ350 ሺህ ብር በማዋጣት ለተማሪዎቹ የቦርሳ ፣ የደብተሮችና ሌሎች የጽህፈት መሣሪያዎች አበርክተውላቸዋል። ድጋፉ በፓርኩ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ታስቦ መደረጉንና በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ሴቶች ፣ ህጻናት ፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የህጻናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ባለሙያ ወይዘሮ አነጋግሪኝ ፈረዱ የከተማው ኅብረተሰብ ከ150 ሺህ ብር ተሰብስቦ  ለ90 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ 10 ልጆች በቋሚነት በየወሩ የ300 ብር ድጋፍ ለማድረግም ወስኗል ብለዋል፡፡ ለአራት ልጆቻቸው ትምሀርት ድጋፍ ያገኙት አቶ ኃይሌ ማሞ  ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ በወቅቱ ባለማሟላታቸው ልጆቻቸው ከትምህርት ይስተጓጎሉ እንደነበር ገልጸዋል።ልጆቻቸው በተደረገላቸው የትምሀርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተጠቅመዉ ጥሩ ዉጤት እንዲያስመዘግቡ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል፡፡ አቶ ጌታነህ ደስታ የተባሉት ወላጅ በበኩላቸዉ ለስደስት ልጆቻቸዉ ለተደረገላቸዉ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል። ልጆቻቸው ለጥሩ ደረጃ እንዲበቁም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡ ድጋፉን ካገኙት ተማሪዎች አንዱ አቤል ግርማ በድጋፍ በተሰጠውን ቁሳቁስ በመረዳትና በርትቶ በማጥናት ቤተሰቡንና አገሩን ለመርዳት እንደሚተጋ ተናግሯል፡፡ በከተማው ወጣቶችና በጎ አድራጊዎች አስተባባሪነት ለተጨማሪ 260 ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን ከከተማው አስተዳደር የሴቶች፣ ህጻናት፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም