በታርጫ ከተማ የተከሰተው የእብድ ውሻ ጉዳት አደረሰ

3704

ጅማ  ግንቦት 11/2010 በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ የእብድ ውሻ በሽታ በመከሰቱ ምክንያት የእንስሳት እርድ ከቆመና ስጋ መብላት ከተከለከለ  ሁለት ሳምንታት እንዳለፈው የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

በበሽታው እስካሁን ድረስ የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉም ተመልክቷል፡፡

የከተማዋ  አስተዳደር ማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ጆቡላ እንደገለጹት የእብድ  ውሻ በሽታ በመከሰቱ ምክንያት የእርድ አገልግሎት በከተማው እንዲቆም ተደርጓል።

ከበሽታው መከሰት ጋር በተያያዘ  ምክንያት በከተማዋ ዙሪያ  የሁለት ታዳጊ ህፃናት ህይወት እንዳለፈ የገለጹት ኃላፊው በበሽታው የተለከፉ የህፃናቱ ቤተሰቦችም በታርጫ ሆስፒታል  የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የታርጫ ከተማ ከንቲባ አቶ አንበሴ ኡሩኩ በበኩላቸው የእርድ አገልግሎት ለጊዜው እንዲቆም የተደረገው ከእብድ ውሻ ወደ እንስሳት  ፣ ከእንስሳት ደግሞ ወደ ሰው  ሊተላለፍ የሚችል በሽታ መከሰቱን በምርመራ በመረጋገጡ ነው “ብለዋል፡፡

በሽታው በሰውና በእንስሳት  ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል ግብረሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

ባለቤት የሌላቸውን  ውሾች ለማስወገድ መርዝ በገበያ ላይ በመጥፋቱ ምክንያት ችግሩ ውስብስብ አድርጎት እንደቆየ ከንቲባው ጠቁመው አሁን ግን አንድ ኪሎ ግራም መርዝ ሀዋሳ ከተማ ላይ በመገኘቱ ውሾችን የማስወገድ ስራው እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ውሾቹን ከተወገዱና በሽታው አለመኖሩን ከተረጋገጠ በኋላ መደበኛው የእርድ አገልግሎት እንደሚጀመርም ከንቲባው አስታውቀዋል።

በታርጫ ከተማ የቃልኪዳን ምግብ ቤት ባለቤት አቶ ታሪክ ኦቦሎ በሰጡት አስተያየት “የእርድ አገልግሎቱ በመቆሙ ምክንያት በገበያችን ላይ መቀዛቀዝ ቢታይም ከጤና በላይ ባለመሆኑ ከስጋ ጋር የተያያዙ ምግቦች ማቅረብ ካቆምን ሁለት ሳምንታት አልፎናል “ብለዋል ።

በከተማዋ በሚገኙ ምግብ ቤቶች “የከብት በሽታ ስለገባ ላልተወሰነ ጊዜ የእርድ አገልግሎት የቆመ መሆኑን እንገልጻለን” የሚል ማስታወቂያ ከሚመለከተው አካል ስልክ ቁጥሮች ጋር አብሮ መለጠፉን የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው ተዘዋውሮ ማረጋገጡን ጭምር ዘግቧል፡፡