ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዋን በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ አቀረበች

242

ጥቅምት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተሞክሮዋን በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ አቀረበች።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከፍተኛ አድናቆት አግኝተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮረው የምስራቅ አፍሪካ መሪዎችና የከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ጉባኤ በጂቡቲ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል።

ጉባኤው "የአየር ንብረት ለውጥና ምርምር ለዘላቂ የመቋቋሚያ መንገድ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።

በጉባኤው ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን በመወከል የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ተገኝተዋል።

የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድና ሌሎችም የአካባቢው ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮችም ተሳትፈዋል።

በጉባኤው የቀጣናው ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ዘላቂ የምርምር መፍትሔዎችን ማፈላለግና በአንድነት መቆም እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣናው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

May be an image of 1 person

ለአብነትም ከጂቡቲ ጋር በታዳሽ ኃይል ልማት ትስስር በመፍጠር ከብክለት የጸዳ ከባቢን ለመፍጠር ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን በማንሳት።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተሞክሮ ለጉባኤው አቅርበዋል።

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች ከ25 ቢሊዮን ያላነሱ ችግኞችን በመትከል ዓርአያነት ያለው እርምጃ መውሰዷን በመጥቀስ።

በየዓመቱ ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯን ቀጣናዊ ለማድረግ እንቅሰቃሴ መጀመሯን ጠቅሰው፤ ጂቡቲን ጨምሮ የተወሰኑ ሀገራት ወደ ተግባር መግባታቸውን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመከላከል እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት በተለይም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተሞክሮዋ በጉባኤው ተሳታፊዎች አድናቆት ተችሮታል።

የኢትዮጵያን መልካም ተሞክሮም በየሀገሮቻቸው በስፋት ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመለገስ በቅንጅት ሶስት ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አከናውናለች።

በዚህም የሁለቱን ሀገራት ትብብር በአረንጓዴ ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም