የሠራዊታችን ቀን

160

ጥቅምት 15/2015 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ጽናት ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ በዱርና በገደል የሚዋደቀው ጀግናው መከላከያ ሠራዊት የሚታሰብበት ቀን ነው።

“ሠራዊት” የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ሲፈቱት “ዐምድ ምሰሶ…” ይሉታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የኢትዮጵያ የአንድነት አምድ የሉዓላዊነት ምሰሶ መሆኑን በቅርብም በሩቅም ጊዜያት በሀገራችን ላይ የተቃጡ ትንኮሳዎችን የቀለበሰበትንና ድል ያስመዘገበባቸው አውደ ውጊያዎች ይመሰክራሉ።

ሀገር በጭንቅ ላይ ስትሆን ተተኪ የሌላት ነፍሱን ለህዝቡና ለሀገሩ በመስጠት በማንኛውም ጊዜና ወቅት ዋጋ ለመክፈል የሚሰራ ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ ይህንንም ሠራዊታችን በሀገራችን ላይ የተቃጡ ትንኮሳዎችን መክቶና ድል አድርጎ አሳይቷል።

ከውጭ ለመጣ ጠላት አልንበረከክም ባይነትና ባንዳን መቅጣት ከመተማ ኡጋዴን፤ ከኡጋዴን እስከ ባድመ የኢትዮጵያ ልጆች አጥንት የተከሰከሰባቸው ስፍራዎች ታሪክ ይናገራል።

የጭቁን ጥቁሮች የብርሃን ቀንዲል የሆነው አድዋ የሠራዊታችንና የህዝባችን የጀግንነት ምስክር ከሆኑት ግንባር ቀደም ክስተቶች አንዱ ሲሆን፤ በወቅቱ ህዝባችን ሀገሬ ተደፈረች ርስቴ ተነካች በማለት ሆ ብሎ የመከላከያ ሠራዊትን ጥቅምና ዋጋ ያስመሰከረበት ድል ነው።

በአድዋ የተመዘገበው ድል በተለያዩ ዘመናት ሲሞከር ለነበረው ዘመናዊ ጦር ግንባታ ብልጭታ የሰጠና በወቅቱ የነበሩ መሪዎች የሰሩበት ኋላም የመጡት አጠናክረው የቀጠሉት ተግባር ነው።

ይልቁንም ከሁለተኛው የፋሽስት ጣልያን የወረራ ሙከራ በኋላ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንስቶ የዘመናዊ ጦር ሠራዊት ግንባታ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሆኗል።

ወታደራዊ መንግስት በነበረው ደርግም ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ነው እስኪባል ድረስ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቱ የሚታወስ ሲሆን አሸባሪውና ባንዳው ህወሓት ወደ ስልጣን ሲመጣ ግን ቀድሞ ማፍረስ የጀመረው ደሙን በዱር በገደል ያፈሰሰውን ወታደር በመበተን ነው።

በስልጣን በቆየባቸው ወቅቶችም የሠራዊትን አንድነት በመከፋፈል የስልጣን እርከኖችን በአንድ ስብስብ ስር በመቆጣጠር ወታደሩን የስልጣኑ አስጠባቂ አድርጎ ለመግዛት ጥሯል።

እጅግ የከፋ የአጥፊነት ተግባሩን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው አረመኔያዊ ጥቃት አረጋግጧል።

ሰብልን ከአንበጣ ሲከላከል፣ ትምህርት ቤት ሲገነባ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ሲያከናውን በነበረ የህዝብ ልጅ ላይ ነው ፋሽስቱ ሕወሃት ጥቃቱን የፈጸመው።

ሠራዊቱ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ 20 ዓመታት ማሳለፉ ሳያንሰው በአሸባሪው ህወሓት የባንዳነት ተግባር ተፈጸመበት።

የጀግኖች አባቶቹ ልጆች የሆነው መከላከያ ሰራዊት የደረሰበትን ጥቃት ቀልብሶ በሳምንታት ውስጥ አሸባሪውን አሽመድምዶ ድልን በመጎናጸፍ ጀግንነቱን አስመስክሯል።

የትግራይ ክልል ህዝብ ተረጋግቶ የግብርና ስራውን እንዲያከናውን ሲባል መንግስት ሠራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣ ቢያደርግም አሸባሪው ግን በጥፋት ተግባሩ በመቀጠል በህዝብ ማዕበል ሁለተኛና ሦሰተኛ ወረራዎችን አካሄደ።

ድል የዘወትር መገለጫው የሆነው የመከላከያ ሠራዊትም በዘመናዊ የውጊያ ስልቶች አሸባሪውን ከመመከት አልፎ ለዘመናት የሰልጣኑ መጠቀሚያ ለማድረግ ሲጥር የነበረውን የትግራይ ክልል ህዝብን ነጻ በማውጣት የሰላም አየር እንዲተነፍስ በማድረግ የህዝብ ልጅነቱን አሳይቷል።

የአለማችን ሃያላን ሀገራት እንደ አይን ብሌን ከሚመለከቷቸው የገዘፈ በጀት ከሚመድቡላቸው ተቋማት መካከል መከላከያ ግንባር ቀደሙ ነው፤ መከላከያን በየትኛውም ሁኔታና አግባብ መደገፍም የዜጎች ግዴታ መሆኑን በሀገራቱ ከጸደቁ ሕጎች መገንዘብ ይቻላል።

እኛም የመከላከያ ሠራዊት ቀንን ስናስብ ሠራዊቱ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ለሀገራችን ጽናት የከፈለውን የደም ዋጋ በመዘከር ሊሆን ይገባል፣ ሠራዊቱ ያለ ስስት ሕይወቱን በመስጠት ያጸናትን ሀገር ከሠራዊቱ ጎን በመቆም፣ በዕውቀት፣ ሐሰተኛ መረጃን በመከላከል፣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ በማድረግ ለሠራዊቱ ያለንን አለኝታነት ማሳየት ይጠበቅብናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም