የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የአህጉሪቱን የውጭ ንግድ እንዲደግፍ መጠቀም ይገባል -ኢሲኤ

509

አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የአህጉሪቱን የውጭ ንግድ በሚደግፍ መልኩ አገልግሎት ላይ መዋል እንደሚገባ ተገለጸ።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ከፍተኛ አመራሮች ሩዋንዳ በቀጣይ አስር ዓመታት በምትመራበት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ውይይት ሲያደርጉ ነው ይህ የተገለጸው።

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሚስተር አንድሪው ሞልድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለአህጉሪቱ የተለየና ወቅታዊ እድል በመሆኑ ከቀጣናው ውጪ ካሉ የንግድ ስምምነቶች የተሻለ ጥቅም ይሰጣል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) መረጃ መሰረት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት 52 በመቶ ያሳድገዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ አገራት መካከል በሚደረግ ንግድ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በማሳደግ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻልና ተወዳዳሪነትን በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ መሰረታዊ እርምጃ ነው።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እውን አንዲሆን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ለአፍሪካ አገራት መንግስታት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት አፍሪካ ወደ ውጭ በምትልካቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች አብዛኛውን ከነጻ ቀጣናው ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት 60 ዓመታት የአፍሪካ ንግድ ከቀረው ዓለም ጋር የሚጠበቀውን ያህል ልዩነት አላመጣም ያሉት ተጠባባቂ ዳሬክተሩ አብዛኞቹ አገራት አሁንም ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ያወሳሉ።

አገራቱ ወደ ውጭ የሚልኳቸው አብዛኞቹ ምርቶችም እሴት ያልተጨመረባቸው በመሆናቸው ትልቅ የንግድ ኪሳራ ውሰጥ እየገቡ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ጥናት መሰረት የአፍሪካ የንግድ ሚዛን ትርፍ በ2012 ከነበረው 24 ቢሊዮን ዶላር በ2016 ወደ 155 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪካ ከውጭ የምታስገባቸው ምርቶች እየቀነሱ መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ትንበያ ቢያሳይም የንግድ ኪሳራን በመቀነስ በኩል አሁንም ሰፊ ስራ እንደሚቀረው ያነሳሉ።

አፍሪካ ከውጭ የምታስገባቸው ሸቀጦችም በ2014 ከነበረው 642 ቢሊዮን ዶላር በ2016 ወደ 501 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱን መረጃው ያሳያል።

የአገራቱ የኢኮኖሚ እድገት ተወዳዳሪነታቸውን እንዳይገታ የማምረቻውን ዘርፍ በማሳደግና ምርታማነትን ለመጨመር የአፍሪካ አገራት በትብብር መስራት ወሳኝ ነው።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ከፍተኛ አመራሮች የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የአህጉሪቱን የውጭ ንግድ የሚደግፍበት ሁኔታ ላይም መምከራቸው ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ከ75 በመቶ በላይ ከአህጉሪቱ ውጭ የተላኩ ምርቶች ማዕድናት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በመሆኑም አህጉሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸውን ምርቶች አይነታቸውን በማብዛት ቀጣይነት ያለው የውጭ ንግድ መሰረት መጣል ይገባታል ተብሏል።