በሃዋሳ ከተማ በመኖሪያ ቤት ቀለም በመቀባት ህዝቡን ለማሸበር የሞከሩ አስር ተጠርጣሪዎች ተያዙ

74
ሀዋሳ መስከረም 14/2011 በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በመኖሪያ ቤቶች ላይ ቀለም በመቀባት በህዝቡ ውስጥ ሽብር ለመንዛት የሞከሩ አስር ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም በከተማዋ ውስጥ የብሄር ግጭት ይነሳል እየተባለ በሚነዛው ወሬ ሳይረበሹ የዕለት ተዕለት ስራቸውን እንዲያከናውኑም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሾዳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በሀዋሳ ከተማ ባለፉት ሦስት ቀናት በታቦር፣ መሀል ከተማና መናኸሪያ ክፍለ ከተሞችና በሌሎች አካባቢዎች በመኖሪያ ቤቶች ላይ ቀለም በመቀባት ህብረተሰቡን የማሸበር ተግባር ተፈጽሟል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ጉዳዩን ለማጥናት ባደረገው ጥረትና በተከናወኑ የጸጥታ ስራዎች በግለሰቦች መኖሪያ ግቢ ላይ የተቀባ ቀለም መኖሩን እንደተረጋገጠ ተናግረዋል፡፡ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ቀይ፣ ነጭ፣ ሰማያዊ፣ ቢጫና ጥቁር ቀለማት እንደተቀቡ የጠቆሙት አቶ ስኳሬ ቀዩ ቀለም የከተማው ማዘጋጃ ቤት ካዳስተር ለመለየት እንደቀባው አመልክተዋል፡፡ በተደረገው ክትትልም እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩትና በቁጥጥር ስር የዋሉት አሥር ሰዎች ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የገለጹት አቶ ስኳሬ፣ ከተያዙት ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት በከተማው በልመና ሥራ ሌሎች ደግሞ በጋራ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ስለታማ መሳሪያዎችን ተጠቅመው አደጋ ለመፈጸም ወደ ከተማዋ የገቡ ጸጉረ ልውጦች እንዳሉና ወደፊት አላማቸው ተረጋግጦ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የጸጥታ ኃይሉና ህዝቡ በመተባባር አካባቢዎችን የመጠበቅ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ቀለም የተደረገባቸው መኖሪያ ቤቶች ልዩነት እንደሌላቸውና በሁሉም ብሔር ተወላጆች መኖሪያ ቤቶች ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የኢዜአ ሪፖርተር በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት በተለያዩ  መኖሪያ ቤቶች ላይ ብሔር ሳይመርጥ ነጭ፣ ቀይ፣ ሰማያዊ፣ ቢጫና ጥቁር ቀለም መቀባቱን ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ የህብረተሰቡን አስተያየት ለመሰብሰብ ጥረት ቢያደርግም "ነዋሪዎቹ ለደህንነታችን እንሰጋለን" በሚል ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም