የተመድ 73ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአንኳር ጉዳዮች ላይ ውይይት ጀመረ

68
አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 ባለፈው ሳምንት የተበሰረው የተባበሩት መንግሥታቱ ደርጅት (ተመድ) 73ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በአንኳር ጉዳዮች ላይ መወያያት ጀምሯል። "የመንግሥታቱ ድርጅት ''ለሁሉም ጥቅም ያለው፤ ለሠላም፣ ለፍትኃዊና ለዘላቂ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ አመራርና የጋራ ኃላፊነት" በሚል መሪ ኃሳብ ይካሄዳል። በዛሬው የድርጅቱ ምልዓተ ጉባኤ ውሎው የኔልሰን ማንዴላ መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በሠላም ላይ ይመክራል ተብሏል። 'የኔልሰን ማንዴላ ጉባኤ' ተብሎ በሚጠራው በዚሁ ሰብሰባ፤ በድርጅቱ ምልዐተ-ጉባኤው ውይይት የተደረገበትን የፖለቲካዊ ድንጋጌ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ድንጋጌ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ከደቡበ አፍሪካና ከአየርላንድ በተውጣጡ ተወካዮች ለአባል አገሮች ትውውቅ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል። በነገው ዕለት ደግሞ በመሪዎች ደረጃ መሪ ኃሳቡን በተመለከተ በደርጅቱ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በሚቀርበው የሠላም ማስከበር ሪፖርት ላይ ጠቅላላ ዓመታዊ ወይይትና ምክክር ተደርጎ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሏል። ምልዐተ ጉባኤው በረቡዕ ዕለትም ዓለም አቀፉን የኑክሌር የጦር መሣሪያ ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ቀንን ለማክበር የማስተዋወቅም ሥራ የሚሰራበት እንደሚሆን ተጠቁሟል። ባለፈው የካቲት ወር ላይ በአባል አገሮች ውይይት ላይ እንዲቀርብ ሥምምነት ላይ የተደረሰበት የሳንባ ነቀርሳ ጉዳይ ለውይይት ይቀረባል ተብሏል። በቀጣይ ሐሙስ ደግሞ ምልዓተ ጉባኤው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተገኘውን ውጤት ይገመግማል ተብሏል። ይሁንና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የጎንዮሽ ሰብሰባዎች "የዓለም ግቦች ሳምንት" እና "የአየር ንብረት ሣምንት በኒው ዮርክ" በሚል መሪ ኃሳብ ይካሄዳል ተብሏል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም