አሸባሪው ህወሓት በክልሎች ሌብነትና ብልሹ አሰራር እንዲንሰራፋ አድርጓል - የሶማሌና የጋምቤላ ክልል የጸረ-ሙስና ኮሚሽነሮች

74

ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ''ታዳጊ'' እያለ በሚጠራቸው ክልሎች በረቀቀ የሙስና ስልት የሕዝብን ሐብትና ንብረት ከመዝረፍ ባለፈ ሌብነትና ብልሹ አሰራር እንዲንሰራፋ ማድረጉን የሶማሌና የጋምቤላ ክልል የጸረ-ሙስና ኮሚሽነሮች ገለጹ።

ኮሚሽነሮቹ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ክልሎቹ በአፈና ውስጥ እንዲወድቁ በማድረግ ሲመዘብርና ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲስፋፉ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሽብር ቡድኑ በተለይም "በክልሎቹ የራሱን ሰዎች በሞግዚትነት በመመደብ የሕዝብን ሐብትና ንብረት ሲዘርፍ ቆይቷል" ሲሉም ነው የጠቀሱት።

የሶማሌ ክልል የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዲ አወል እንደገለጹት፤ በክልሉ የህዝቡን ኑሮ የሚቀይሩ በርካታ ሃብቶች ቢኖሩም በአሸባሪው ህወሃት የስልጣን ዘመን ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል።

በተለይ የሶማሌ ክልል ህዝብ ሲፈጸሙበት የነበሩ የህግ ጥሰቶችን እንዳያጋልጥ በአፈናና ጭቆና ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት አሸባሪው ህወሓት የሱማሌ ክልል ሃብትን በመዝረፍ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል መፈጸሙንና ክልሉን ማራቆቱን ተከትሎ በህዝቡ ላይ የማይሽር ጠባሳ አስቀምጧል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከለውጡ ማግስት የክልሉ መንግስት በወሰዳቸው እርምጃዎች አበረታች ውጤቶች እየመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ተላላኪ በነበሩ አመራሮች ላይ የተወሰደው የተጠያቂነት እርምጃ አስተማሪና ተምሳሌት እንደሆነም አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ትኩረቱን ወደ ልማት ማዞሩን ጠቅሰው፤ ሀገርን በጋራ የማሳደግና ከልማቱም በፍትሐዊነት የመጠቀም ዝንባሌ እየዳበረ መጥቷል ነው ያሉት።

የጋምቤላ ክልል የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳይመን ቶሪያል በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ቆይታው የክልሉን ሃብት በመበዝበዝ የህዝቡ የልማት ጥያቄ እንዳይመለስ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑ የህዝብና የመንግስት ሀብት የሆነውን መሬት በልማት ሽፋን ከግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን ያለአግባብ ሲጠቀምበት እንደነበር ጠቁመዋል።

"የክልሉ ህዝብ በቂ እውቀት የሌለውና የበታች እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች በመግለጽና ለማሳጣት በመሞከር፤ እንዲሁም ጫና በማሳደር የሙስና ወንጀል እንዲንሰራፋ አድርጓል" ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።

ባለፉት አራት ዓመታት በተወሰዱ የሪፎርም ስራዎች ለውጥ ካስመዘገቡ ክልሎች አንዱ የጋምቤላ ክልል መሆኑን ገልጸው፤ ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሰራሮች እንዲሻሻሉ ተደርጓል ብለዋል።

በተለይም የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮችን ከአስፈጻሚው አካል በማውጣት በቀጥታ በክልሉ ምክር ቤት እንዲመሩ መደረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የአካባቢውን እምቅ ሐብት በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል የተረጋገጠበት ወቅት ላይ መደረሱን ገልጸው፤ በህዝቡና በአመራሩ ዘንድ መነቃቃትና አብሮ የመስራት ፍላጎት መኖሩን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ሙስናና ሌብነትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠርና የነበረውን አስከፊ ሁኔታ ላለመድገም ኮሚሽኑ የሙስና ተጋላጭነትን መከላከል ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም