በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ሰፊ የውይይት መድረኮች ይዘጋጃሉ-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

151
አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 በዜጎች መካከል ብሄራዊ መግባባት የተደረሰበት ሰንደቅ ዓላማ እንዲኖር ለማድረግ በቀጣይ ሰፊ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። ምክር ቤቱ ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2011 "ሰንደቅ ዓላማችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት አድርጎ በመጠቀም ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይሆነኛል የሚለውን የተሻለ ሰንደቅ ዓላማ ካቀረበ ለማሻሻል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በማክበር የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረት ቢደረግም በቂ ባለመሆኑ ልዩነቶች ተፈጥረው የግጭት መንስኤ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም በሰንደቅ ዓላማ መካከል ያለው ልዩነት የጸብና የግጭት መንስኤ ከማድረግ ይልቅ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለ ሃሳብ ማፍለቂያ ማድረጉ ይበጃል ብለዋል። ኢትዮጵያ "ብሄራዊ መግባባት የተፈጠረበትና አንድ ወጥ መገለጫ ሰንደቅ ዓላማ ሊኖራት ይገባል" ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔዋ አሁን ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የመመያያ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። እስካሁን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ኅብረተሰቡ በህገ መንግስቱ የጸደቀውን ይዞ ይወጣ ስለነበር ልዩነት እንዳለው በአግባቡ አለመረዳታችን አሁ ላለው ሰፊ ልዩነት ዳርጎናል ብለዋል። በመሆኑም የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ባንዲራ ከማውለብለብ ባለፈ በሁሉም ዘርፎች ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት ሁሉም የተግባባበት ሰንደቅ ዓላማ እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል። ኅብረተሰቡ ያመነበትና ይሆነኛል ያለውን ከመረጠ ሰንደቅ ዓላማው ህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የማይሻሻልበት ምክንያት እንደሌለም ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም