የገነቡትን ፍቅር ጠብቀው በማቆየት አገራዊ ለውጡን ዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ የድሬዳዋ ገንደ ተስፋ ነዋሪዎች ገለጹ

92
ድሬዳዋ መስከረም 13/2011 የፀረ- ሰላም ሃይሎችን ድብቅ አጀንዳ ነቅተው በመከላከልና ለዘመናት የገነቡትን ፍቅር በማቆየት የተጀመረውን አገራዊ የለውጥ ሂደት ከዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ የድሬዳዋ ገንደ ተስፋ ወጣቶችና ነዋሪዎች ተናገሩ። ወጣቶቹ ከፖሊስ ጋር በመስራትና ድብቅ አጀንዳ ያነገቡ አካላትን ሴራ በማክሸፍ ለአካባቢያቸው ለሰላም መስፈን ግንባር ደቀም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልፀዋል፡፡ በድሬዳዋ ልዩ ስሙ ገንደ ተስፋ በተባለ አካባቢ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ማንነታቸው ለጊዜው ባልታወቁ አካላት ልዩ የቀለም ምልክት መቀባትን ተከትሎ  በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት እዚህም ሊፈጠር ይሆን በሚል ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት ውይይት ያደረጉት የአካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎች በድሬዳዋ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት የገነቡት ፍቅር ድብቅ አላማን ባነገቡ ፀረ-ሰላም አካላት ሴራ እንደማይደናቀፍ ተናግረዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዮናስ ከበደ "በገንደ ተስፋም ሆነ በአካባቢው ስጋት ለመፍጠርና የነዋሪውን የእርስ በርስ ፍቅር ጥርጣሬ ላይ ለመጣል  በመኖሪያ ቤቶች ላይ ምልክት በማድረግ አንድነትን ስጋት ላይ የሚጥሉ አካላትን በጋራ ተባብረን ለፍትህ እናቀርባለን" ብለዋል፡፡ "ድርጊቱ አገራዊ ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ አካላት ተግባር ነው" ያለው ወጣት በሐር አብዱላሂ በበኩሉ ድርጊቱ ወጣቶችንም ሆነ አቃፊና ደጋፊውን የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክል ተናግሯል። "በፍቅርና በአንድነት ተረዳድቶ የሚኖረውን የድሬዳዋ ህዝብ ለማጋጨትና ሽብር ለመፍጠር የሚደረገው ተንኮል መቼም አይሳካም" ሲልም ገልጿል፡፡ "ሁላችንም ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅተን በመስራትና ተባብረን በመስራት የአካባቢያችንን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን" ያሉት ደግሞ አቶ ስንታየሁ ከተማ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ የአካባቢው ወጣቶች ከህብረተሰቡ ጋር በፍቅርና በደስታ፣ በሀዘንና በችግር የማይለዩ መሆናቸውን ገልጸው "ድርጊቱ የሀገሪቱን ወቅታዊ ችግሮች ምክንያት በማድረግ የድሬዳዋን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረግ ጥረት ነው" ብለዋል፡፡ "አብረን እየኖርን ያሉ ወጣቶች ጥቃት አይፈጽሙብንም" ያሉት ወይዘሮ መዲ ገብሬ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፣ " ይህን ብናውቅም  በተፈጠረው ውዥንብር ተደናግጠን ለአንድ ቀን በቤታችን አላደርንም፤ አሁን በጋራ መወያየታችን ትልቅ እፎይታን ፈጥሮልኛል" ብለዋል፡፡ " እኔና አማራ ጓደኛዬ የሁለታችንንም እናቶች ጡት በየተራ እየጠባን ነው ያደግነው፤ አሁንም አብረን ያለን ወጣቶች ነን፤ የትኛውም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚጠነሰሰው ሴራ እኛንም ሆነ በድሬዳዋ ተሳስበው በፍቅር በሚኖሩ ዜጎች ዘንድ ዋጋ የለውም " ያለው ደግሞ ወጣት ኤሊያስ መሐመድ ነው፡፡ በአካባቢው በሚገኙና 56 በሚሆኑ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ቤቶች ላይ ምልክት ተደርጎ እንደነበር ጠቁሞ፣ ይህን የጥፋት ተግባር በመፈጸም  የቄሮና የኦሮሞን ስም ለማጥፋት የሚሯሯጡና ድብቅ ዓላማ ያላቸው አካላትን ለይተው ለህግ አሳልፈው እንደሚሰጡ ተናግሯል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የሳቢያን ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኮማንደር መከተ ማሞ በቤቶች ላይ ምልክት የተደረገው በገንደ ተስፋ ብቻ ሳይሆን በቦረን፣ በጎሮ፣ በሰባተኛና ሌሎች የድሬዳዋ አካባቢዎች ጭምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በነዋሪዎች መካከል ውዥንብር ወሬ በመፍጠር ድብቅ ዓላማን ለማሳካት የሚደረግ ጥረት መቼም ቢሆን እንደማይሳካ ተናግረው "ፖሊስ ያለበትን ከፍተት በመድፈንና ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅትም ድርጊቱን የፈጸሙትን ተከታትሎ በማጥራት ለህግ የማቅረብ ሥራ በመስራት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የሳቢያን ቀበሌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ በሻ በበኩላቸው የተፈፀመው ድርጊት ዘርና ብሔርን እንደማይወክል ገልፀዋል። የኦሮሞ ህዝብና ወጣቱ በሀገሪቱ ለተገኘው ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦና መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰው፣ "ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የሚደረጉት ጥረቶች በሰከነ መንፈስና በውይይት መፍታት ይገባል" ብለዋል፡፡ በተለይ ወጣቱ ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መስራት እንዳለበት ገልጸው፣ ህብረተሰቡም በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን መነዳት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም