የዳቦ ዱቄት እጥረት ችግር ፈጥሮብናል- የገንዳ ውሃ ከተማ ዳቦ ቤቶች

64
መተማ  መስከረም 13/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በወር የተፈቀደላቸውን የዳቦ ዱቄት ኮታ በአግባቡ  አለማግኘታቸው በስራቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን በከተማው በዳቦ ጋገራና ማከፋፈል ሥራ የተሰማሩ ወጣቶችና ባለሀብቶች ተናገሩ፡፡ ለዳቦ ጋጋሪዎቹ እየቀረበ ያለው የዱቄት መጠን አነስተኛ መሆኑ ታውቆ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። አለንጓና ጓደኞቻቸው ዳቦ መጋገርና ማከፋፈል ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አለባቸው ማሞ ለኢዜአ እንደተናገረው የተፈቀደላቸው የዳቦ ዱቄት መጠን አነስተኛ ቢሆንም ያንኑ በአግባቡ ማግኘት ባለመቻላቸው ማህበሩ ለኪሳራ እየተዳረገ ነው። 16 ሆነው በማህበር በመደራጀት ከልማት ባንክ በብድር ባገኙት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር የዳቦ መጋገሪያ ቤት ከፍተው ሥራቸውን ቢጀምሩም በዱቄት እጥረት ምክንያት ስራቸው እንቅፋት እንደገጠመው ተናግሯል። ዘመናዊ የዳቦ መጋገሪያ ማሽኑ በቀን 18 ኩንታል ዱቄት ዳቦ መጋገር የሚችል ቢሆንም በወር ከ40 ኩንታል ያልበለጠ ዱቄት ብቻ እየቀረበላቸው በመሆኑ መቸገራቸውን ገልጸዋል። ወጣት አለባቸው እንዳለው በከተማ አስተዳደሩ በወር 82 ኩንታል የተመደበላቸው ቢሆንም አሁን እየደረሳቸው ያለው ከግማሽ በታች ነው። በእዚህም በየወሩ ለአንድ ሳምንት ጊዜ ያህል አባላቱ ያለስራ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ አመልክቷል። "ችግሩ የማህበሩን አባላት ብቻ ሳይሆን በቁርስ ቤት ለተሰማሩ ግለሰቦች ጭምር ጫና አለው" ያለው ወጣቱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡ ሌላው በዳቦ መጋገርና ማከፋፈል ሥራ የተሰማሩት ሼክ ከድር ኡስማን በበኩላቸው በከተማዋ የዱቄት እጥረት በመኖሩ ለደንበኞቻቸው ዳቦ በወቅቱ ማድረስ ባለመቻላቸው ቅሬታ እየተፈጠረ መሆኑንና ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ ለመክፈል መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ " በስራዬ ለመንግስት ግብር መክፈል ግዴታዬ ቢሆንም በዱቄት እጥረት ምክንያት ግብሬን በአግባቡ ለመክፈል እየተቸገርኩ ነው። ሥራ ሲቆምም የሥራ ዕድል የፈጠርኩላቸው ልጆች ይበተናሉ" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡ በገንዳ ውሃ ከተማ ቀበሌ 02 በዳቦ መጋገርና ማከፋፈል ሥራ የተሰማሩት አቶ ኡስማን ኢብራሂም በበኩላቸው በከተማዋ ባለው የዱቄት እጥረት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ሥራ ማቆማቸውንና በዚህም ለኪሳራ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በቁርስ ቤት ንግድ ሥራ የተሰማራችው ወጣት እየሩሳሌም አያናው በበኩሏ በከተማዋ ያሉ ዳቦ ቤቶች መጋገር በማቆማቸው በስራዋ ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባት ተናግራለች፡፡ የገንዳ ውሃ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አዱኛ አለሙ በበኩላቸው ለከተማዋ የተፈቀደ የዱቄት መጠን በወር 190 ኩንታል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። መጠኑ በቂ ካለመሆኑ በተጨማሪ አንዳንዴ የሚቀርበው ከተመደበው ከግማሽ በታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "የዱቄት እጥረቱ በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለ ችግር ነው" ያሉት ወይዘሮ አዱኛ፣ ለከተማው የተፈቀደው የዱቄት ኮታ መጠን አነስተኛ መሆኑ ታውቆ እንዲሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በከተማዋ በማህበር ከተደራጁ ወጣቶች በተጨማሪ ስድስት ባለሀብቶች በዳቦ መጋገርና ማከፋፈል ሥራ ተሰማርተዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም