ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ

154
አዳሚ ቱሉ መስከረም 13/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቡልቡላ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ። የቡልቡላ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ በ263 ሄክታር መሬት ላይ ነው እየተገነባ የሚገኘው። የፓርኩ የመሰረት ድንጋይ ነሃሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ መቀመጡ ይታወሳል። ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጎበኘው ይህ ፓርክ አጠቃላይ ወጪው ሰባት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስና ግንባታው በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርኩ አስተባባሪ ለኢዜአ ተናግረዋል። አስተባባሪው ኢንጂነር ሃቢብ ቁምቢ እንዳሉት ግንባታው በሶስት ምዕራፍ በመካሄድ ላይ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛው ዙር 53 በመቶ ሲደርስ የሶስተኛው ምዕራፍ ግንባታም ተጀምሯል። ፓርኩ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ወደ ፋብሪካ ገብተው ተጨማሪ እሴቶች ተጨምሮባቸው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት ነው። በአገር ውስጥ የስራ ተቋራጭ እየተሰራ ያለው ይህ ፓርክ በአሁኑ ወቅት ለ1 ሺህ 700 ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ሲጠናቀቅ ከ15 እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። በውስጡ 100 ሼዶች ይኖሩታል ተብሎ ሲጠበቅ እስከ 400 ፋብሪካዎች እንደሚይይዝም አስተባባሪው ተናግረዋል። ኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ ሲጀምር ከሻሸመኔ የገጠር ሽግግር ማዕከል አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማር እና የእንስሳት ውጤቶችን በግብዓትነት ይቀበላል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም