በደቡብ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከደን ልማትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ የወጡ ደንብና ህጎችን ለማስፈፀም በትኩረት ይሰራል-ቢሮው

102

ሀዋሳ ጥቅምት 10/2015(ኢዜአ) በደቡብ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከደን ልማት፣ ከቆሻሻ አወጋገድና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተይይዞ የወጡ ደንብና ህጎችን ለማስፈፀም በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የዘርፉን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ጉባኤ ያካሄደ ሲሆን በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ  የቢሮው ኃላፊ ዳንኤል ዳምጠው እንዳሉት ሁሉም ሰው ንጹህ እና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው በሀገሪቱ ህገ መንግስት ተደንግጓል።

"ይሁንና ህጉ በአግባቡ ተግባራዊ ባለመደረጉ ህብረተሰቡ ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻን በዘፈቀደ የሚያስወግድበት ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል" ብለዋል።

ችግሩን ለማስወገድ ቢሮው ባለፈው ዓመት በቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ ለህብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራቱን አመልክተዋል።

ሆኖም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ "በተያዘው በጀት ዓመት ከደን ልማትና ጥበቃ ሥራው ጋር በማስተሳሰር በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትንና በአካባቢ ጥበቃ የወጡ ደንብና ህጎችን ለማስፈፀም አበክሮ ይሰራል" ብለዋል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ለደን ልማትና ጥበቃ ሥራው ተገቢ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ ህግ አተገባበር ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረቶም ባርጋ በበኩላቸው፣ በዞኑ ያለው የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ባለመተግበሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው ብለዋል።

በዘፈቀደ የሚወገድ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ሰዎችና እንስሳትን በተለያየ መንገድ ለብክለት በመዳረግ በጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዜጎችን ፅዱና ውብ በሆነ ቦታ የመኖር ህገመንግስታዊ መብት ለማስጠበቅ የወጣውን አዋጅ በዞኑ በማስተግበር በቆሻሻ አወጋገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ምህረቶም ተናግረዋል

ከቄራ ንፅህና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ በዞናቸው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርአቱ የጎላ ክፍተት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መርክነህ ማለዳ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ 3 የሪፎርም ከተሞች ያለው የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የዜጎችን በጤና የመኖር ህገ መንግስታዊ መብት ያገናዘበ አይደለም።

ቢሮው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ችግሩ በማህበረሰቡ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተሞቹ ለደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ የቦታ ለውጥ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ መርክነህ ተናግረዋል።

"ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ጥናቶችን ለማካሄድ ከሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም