በምዕራብ ሸዋ ዞን በስንዴ ቡቃያ ላይ የተከሰተውን የዋግ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው

61
አምቦ መስከረም 13/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን በስንዴ ቡቃያ ላይ ተከስቶ የነበረውን የዋግ በሽታ በአርሶአደሮች ርብርብ በአብዛኛው መቆጣጠር እንደተቻለ የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በዞኑ በደንዲና ኤጀርሳ ለፎ ወረዳዎች የሚገኙ አንዳንድ አርሶአደሮች በበኩላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በሽታው በሰብላቸው ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በቡድን ተደራጅተው የፀረ ዋግ መድኃኒት በመርጨት እየተከላከሉ መሆኑን ተናግረዋል ። የምእራብ ሸዋ ዞን  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የአዝእርት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ደጉ ረጋሳ እንደገለጹት በዞኑ ካለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአራት ወረዳዎች በ4 ሺህ 553 ሄክታር መሬት ላይ በተዘራው የስንዴ ቡቃያ ላይ የዋግ በሽታ ተከስቶ ነበር ። የግብርና ባለሙያዎችና አርሶአደሮች ባደረጉት የተቀናጀ ርብርብ እስካሁን ድረስ ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን ከበሽታው ነፃ ማድረግ ተችሏል ። የዋግ በሽታውን ለመቆጣጠር 2 ሺህ 500 ሊትር  የፀረ ዋግ በሽታ መድኃኒት ርጭት የተካሄደ ሲሆን በመቆጣጠር ስራውም በልማት ቡድን የተደራጁ 4 ሺህ 769 አርሶአደሮች ተሳትፈዋል ። ባለሙያው እንዳሉት፣ በሽታው በታየባቸው ደንዲ፣ ኤጀርሰ ለፎ፣ ኤጄሬና ሊበን ጃዊ ወረዳዎች በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠርና በአዳዲስ ማሳዎች ላይ እንዳይስፋፋ ለማድረግ አርሶ አደሩ በባለሙያዎች ድጋፍ የታገዘ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። የደንዲ ወረዳ  አርሶ አደር ያደሳ ቡልቲ  በሰጡት አስተያየት ከግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ሙያዊ ምክርና ድጋፍ በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የስንዴ ቡቃያቸው ለከፋ ጉዳት ሳይዳረግ መቆጣጠር እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የእዚሁ ወረዳ አርሶአደር ዲልጋሱ ፈከንሳ በበኩላቸው "በሽታው ተከስቶ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በየቀኑ ማሳዬን በመፈተሽ የመከላከል ሥራ እየሰራሁ እገኛለሁ" ብለዋል ። የፀረ ዋግ በሽታ መድኃኒት በመርጨት በሽታው በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል በተደረገው ጥረት የባለሙያዎች ምክርና እገዛ ፋይዳው የጎላ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ አርሶ አደር በላይ መንግስቱ ናቸው። ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2010/ 2011 የመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከ615 ሺህ ሄክታር መሬት ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም