በፍትህ ተቋማት የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የነቃ የህዝብ ተሳትፎን ማጎልበት ይገባል

577

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 የነቃ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበትና ተጠያቂነትን በማስፈን በፍትህ ተቋማት የሚታዩ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ ተናገሩ።

“ጠንካራ የፍትህ ተቋማት ለአስተማማኝ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ” በሚል የፍትህ አካላት አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በዛሬው እለት ተካሂዷል።

በዚህ ጊዜ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ እንደገለጹት፤ በፍትህ ተቋማት ውስጥ ስፋትና ጥልቀታቸው የተለያዩ ችግሮች ይስተዋላሉ።

‘ሙስና፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር ወይም መልቀቅ፣ የተንዛዛ የቀጠሮ ምልልስ መኖር በዋናነት ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው’ ብለዋል።

በቀጣይ ሁሉም የፍትህ ተቋማቱን ችግሮች ለመፍታት ህዝብ የመከረባቸውንና ቅሬታ ያቀረበባቸውን ጉዳዮች በበቂ አደረጃጀትና አመለካከት የተደገፈ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለመፍትሄ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የህዝብ ተሳትፎን ማጎልበትና ተጠያቂነትን የሚያሰፈኑ ሥራዎችን ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግም ጨምረው ገልጸዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሰው ሃብትና ኢንዶክትርኔሽን ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ያረጋል አደመ በበኩላቸው፤ ፖሊስ የሚሰራው ወንጀል የመከላከልና የምርመራ ተግባር የተሳካ እንዲሆን ህብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል፣ ለማጣራት፣ የተጣሩ የምርመራ መዝገቦችን ለሚመለከታቸው አካላት ለማቅረብ፣ አንድ ሰው ወንጀለኛ ተብሎ በማረሚያ ቤት በሚቆይበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይደርሰበት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በወንጀል ተፈርዶበት የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከማረሚያ ቤት የሚወጣ ታራሚ አምራች ዜጋ እንዲሆንም ከሚመለታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የፖሊስ ተግባራት ቀልጣፋ እንዲሆኑ ዘመኑን የሚመጥኑ ስልጠናዎችን ለመስጠት ኮሚሽኑ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ማዕከላትን ከፍቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው የፍትህ ስርዓቱን የበለጠ ለማጎልበት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘርይሁን ጴጥሮስ “የፍትህ ተቋማት ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ ተግባራትን በማከናወን ቀልጣፋና አስተማማኝ ፍትህ መስጠት ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይ ቋሚ ኮሚቴው ቀልጣፋና ውጤታማ የፍትህ ስርዓት እንዲጎለብት የሚያደርገውን የድጋፍ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በፍትህ ተቋማት ውስጥ የሚመለከታቸውንና የሚታዘባቸው ችግሮች እንዲቀረፉ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ አቶ ዘርይሁን ጠይቀዋል።