ከጅቡቲ ወደ አዲስ አባበ ሲጓዝ በነበረ ባቡር 19 ግመሎች ተገጭተው ሞቱ

212
አዳማ መስከረም 13/2011 ከጅቡቲ ወደ አዲስ አባበ 250 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ በነበረ ባቡር 19 ግመሎች ተገጭተው መሞታቸውን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ ገለጸ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ እንደገለጹት ባቡሩ ትናንት ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ ግመሎቹን የገጨው በፈንታሌ ወረዳ ኧጋ ሄዱ በተባለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው። በባቡሩ ተገጭተው የሞቱት 19 ግመሎች ሲሆኑ ሌሎች ሦስት ግመሎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ኮማንደሩ ገልጸዋል። "ለጉዳቱ የተዳረጉት ሁሉም ግመሎች 750 ሺህ ብር ይገመታሉ" ያሉት ኮማንደሩ በአደጋው ምክንያት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ በባቡሩ ውስጥ የነበሩ 250 መንገደኞች ከባቡሩ ሳይወጡ ለ20 ሰዓታት መቆየታቸውን ገልጸዋል። የምድር ባቡር ድርጅት ለግመሎቹ ካሳ ለመክፈል በመስማማቱ የሞቱትን ግመሎች ከሃዲዱ ላይ በማንሳት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ባቡሩ ወደአዲስ አበባ ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል። አካባቢው የአርብቶ አደሮች መኖሪያ በመሆኑ ባለፈው ዓመት አጋማሽም በተመሳሳይ ሁኔታ 300 ፍየሎች በባቡር ተገጭተው እንደነበረም አስታውሰዋል። በበሰቃ ሐይቅ አካባቢ ያለው የባቡር ሀዲድ የሰዎችና የእንስሳት ማቋረጫ መንገድ የሌለውና በአጥር የተከለለ ባለመሆኑ የምድር ባቡር ሠራተኞችም ሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኮማንደር አስቻለው አለሙ መክረዋል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሸን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ተጠይቀው ጉዳዩ ኮርፖሬሽኑን ሳይሆን የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ኩባንያን እንደሚመለከት ገልጸዋል። የኩባንያውን የህዝብ ግንኙነት ስልክ ለማገግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም