ለዱር እንስሳት መብት ተቆርቋሪ ትውልድ በመፍጠር ፓርኮችን ከአደጋ መታደግ ይገባል

161
አዲስ አበባ መስከረም 13/2011 ለዱር እንስሳት መብት ተቆርቋሪ ትውልድ በመፍጠር ብሔራዊ ፓርኮችን ከተደቀነባቸው አደጋ መታደግ ይገባል ተባለ። ከፍተኛ ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ ብሔራዊ ፓርኮች እንዲያገግሙ ለማድረግ ውስጣዊና ውጫዊ አቅምን ማጎልበትና መጠቀም እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቁሟል። በምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን፣ የባህልና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደተናገሩት አደጋ የተጋረጠባቸውን ፓርኮች ለመታደግ ለዱር እንስሳት መብትና ጥቅም መከበር የሚተጋ ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል። ወቅቱ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚሰሩ ዜጎች እየተፈጠሩበት መሆኑን አውስተው ይህን ልምድ በዱር እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤም መድገም ይገባል ብለዋል። በቂ ኃብት መመደብ፣ አካባቢን መሰረት ያደረገ ጥናት ላይ የተመሰረተ ሠነድ ማዘጋጀትም ፓርኮቹን ለመታደግ ሁነኛ መፍትሄዎች ናቸው ሲሉ ጠቁመዋል። ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው ተብለው ከተለዩት ፓርኮች መካከል ኦሞ፣ አቢያታ ሻላ፣ ጋምቤላና ባቢሌ እንዲያገግሙ ለማድረግ ውስጣዊና ውጫዊ አቅሞችን መጠቀም ተገቢ መሆኑንም አክለዋል። ለዚህም ቋሚ ኮሚቴው የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር መስፍን አረጋግጠዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማኅበራዊ ሴክተር እቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ኤርጋይ በበኩላቸው በፓርኮች አካባቢ የሚካሄዱ የልማትና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። የልማት ሥራዎች በፓርኮች ደኅንነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማያሳድር መልኩ ተጣጥመውና ተናበው መከናወን አለባቸውም ብለዋል። የፓርኮቹና የልማት ሥራዎች ዕቅዶች የመናበብ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት በፕሮጀክትና በፖሊሲዎች ላይ ተግባቦት ፈጥረው መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ዘርፉን በማጠናከር ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም ሕጎችን የመፈተሽና የማሻሻል ሥራ መከናወን ያስፈልጋል ሲሉም አቶ ወንድሙ ተናግረዋል ። በኢትዮጵያ 27 ብሔራዊ ፓርኮች ይገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም