በደቡብ ክልል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በጤና አገልግሎቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አላስከተለም---የክልሉ ጤና ቢሮ

134
ሃዋሳ መስከረም 13/2011 በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በጤና ስራው ላይ ከፈጠረው ጫና ባለፈ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳላስከተለ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው በ2010 ዓ.ም የጤናው ሴክተርና በ2011 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ መክሯል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አብርሀም አላና አንዳሉት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ለወራት መቆየታቸው በጤና ስራው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አላስከተለም፡፡ በመጠለያ ጣቢያዎቹ የነበረው መጨናነቅ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ወባ፣ አተትና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ ይከሰታል የሚል ስጋት ቢያድርም አስከፊ የጤና ችግር አለማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡ ቢሮው ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚንስቴርና የጤና ልማት አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ሰባት ተንቀሳቃሽ የህክምና ማዕከላትን በመክፈት ለተፈናቃዮቹ ተገቢውን የጤና አገልግሎት መሰጠቱን ነው የተናገሩት፡፡ በቅንጅት በተከናወነው ተግባር ወረርሽኝ እንዳልተከሰተና በክልሉ የጤና ስራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳላስከተለም አስታውቀዋል፡፡ በዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ መርሃ ግብርና የአጋሮች መድረክ አስተባባሪ አቶ አገኘሁ ገብሩ እንዳሉት ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዜጎችን የመደገፍና የህክምና አገልግሎት የመስጠቱን ስራ አጋር ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመቆም ባከናወኑት ተግባር ውስብስብ የጤና ችግር እንዳይከሰት ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ብዙ ተፈናቃይ በነበረበት ጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የዶዶሮ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ወይዘሪት ብዟየሁ ጴጥሮስ እንዳለችው ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የነበረው ስራ በአብዛኛው በመጠለያ ጣቢያዎች ላሉ ተፈናቃዮች ትኩረት በመሰጠቱ ጫናው ከባድ ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ መደበኛው የጤና ኤክስቴንሽን ስራ ቀደም ባሉት ወራት ሲሰራ ከነበረው አንጻር ባለመሰራቱ አፈጻጸሙን ዝቅተኛ እንዳደረገው ተናግራለች፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም