ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ አድርገዋል...የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

70
መቀሌ ግንቦት 11/2010 መንግስት ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመጀመሩ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃና የግሉ ዘርፍም ወደ ውድድር እንዲገባ እያደረገው ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ። በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ታደሰ መዝገቦ እንዳሉት ከአስር አመታት በፊት በባንኮች የብድር ፈላጊ ደንበኞች ቁጥርና ፍላጎት ውስን ነበር። "መንግስት በልማት ላይ በስፋት እጁን በማስገባቱ ግን ተቀዛቅዞ የነበረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ አድርጎታል" ብለዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከባንኮች ብድር ለማግኘት በወረፋ የማድረግ አስገዳጅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መፈጠሩን አስረድተው ይሔም የግሉን ሴክተር ወደ ውድድር ያስገባ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ያከናወነው ተግባርና ያስገኘው ለውጥ ኢኮኖሚውን ያነቃቃው በመሆኑ በባንኮች የሚገኘው ተቀማጭ ገንዘብ ጥቅም ላይ እንዲውል እንዳደረገውም አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈ መንግስት በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የሰራውን ያህል የሰብል ምርታመነትን በማሳደግ ረገድ ከዘመቻ የተለየ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነገር አለመታየቱን ረዳት ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል። በምግብ ሰብሎች ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት ደሞዝ ከመጨመር ይልቅ ምርታማነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል። "በመንግስት የሚካሔዱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ድህነት ከመቀነስ ባለፈ ሀገሪቱ በአለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሚያደርጉዋት ናቸው" ያሉት ደግሞ ሌላው የምጣኔ ሀብቱ ምሁር ዶክተር ሀፍቶም ባይራይ ናቸው። በሜጋ ፕሮጀክቶች የሚገኝ ጥቅምም ሌሎች ኢንዱስትሪዎች በተለይም ድህነትን ለማቃለል የሚሰራባቸው ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዙ ተናግረዋል። እንደ ስኳር ፕሮጀክቶች ያሉት ደግሞ በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄዳቸው ሌላ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው የአንዱ መጓተት የሌላውንም ልማት እንደሚያደናቅፍ አስረድተዋል። በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብትና የሂሳብ አያያዝ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር አርአያ ሓጎስ በበኩላቸው "ሜጋ ፕሮጀክቶቹ የግል ባለሃብቶችን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ግለሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው" ብለዋል። ህብረተሰቡም እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች የለውጥ ተስፋ በማድረግ በግንባታው ሒደት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ለዚህም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚታየው ርብርብ ጉልህ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል። የተጀመረው ልማት በተፈለገው መንገድ ውጤታማ እንዲሆንም "መንግስት አሁን ደግሞ ወጣቱ ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም