በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ፈረንሳይ ትደግፋለች - አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ

217

ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት የፈረንሳይ መንግስት እንደሚደግፈው በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ተናገሩ።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በአገራዊ ምክክር ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት የምታደርገውን ጥረት ያደነቁት አምባሳደሩ፤ ለግጭት መፍትሄው ወታደራዊ ሃይል ሳይሆን ሰላማዊ ንግግሮች በመሆናቸው የሰላም ሂደቱ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት እንዳላት አስታውሰው፤ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዙሪያ የትብብር ግንኙነቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት የፈረንሳይ መንግስት የሚደገፍ መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በበኩላቸው የፌዴራሉ መንግስት ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ የሰጠ ቢሆንም በአሸባሪው ህወሃት በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ የቆየ መሆኑን ለአምባሳደሩ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት አሁንም የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ ሂደት ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ የፈረንሳይ መንግስት፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አካላት በአሸባሪው ህወሃት ላይ ጫና በመፍጠር ለሰላም አማራጭ ዝግጁ እንዲሆን እንዲሰሩ ጠይቀዋል። 

አሸባሪው ህወሃት ለሰላማዊ ውይይቱ ቀና ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ መንግስት ሁል ጊዜም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ዝግጁ ሆኖ ምቹ ሁኔታዎችን እየጠበቀ መሆኑን በማንሳት የፈረንሳይ መንግስትም ድጋፍ እንዲያደረግ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አካታች  አገራዊ ምክክር ፈረንሳይ የምትደግፍ መሆኑን አምባሳደሩ መግለጻቸውን ምክትል ፕሬዝዳቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም